ክሬምሊን የአሳድ ሚስት የፍቺ ጥያቄ አቅርበዋል መባሉን አስተባበለ
የአሳድ ሀብት እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል በሚል የወጡ ዘገባዎችም መሰረተ ቢስ ናቸው ብለዋል ቃል አቀባዩ ዲሚትሪ ፔስኮቭ

አስማ አል አሳድ የብሪታንያ እና ሶሪያ ዜግነት ቢኖራቸውም ለንደን የአሳድ ቤተሰቦችን እንደማታስጠልል ማስታወቋ ይታወሳል
ሩሲያ የአሳድ ሚስት የፍቺ ጥያቄ አቅርበዋል መባሉን አስተባበለች።
የቱርክ መገናኛ ብዙሃን የቀድሞዋ የሶሪያ ቀዳማዊት እመቤት አስማ አል አሳድ ከበሽር አል አሳድ ጋር በፍቺ ተለያይተው ከሩሲያ መውጣት ይፈልጋሉ የሚል ዘገባ አውጥተው ነበር።
በጉዳዩ ዙሪያ የተጠየቁት የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ “መረጃው ከእውነት የራቀ ነው” በሚል ውድቅ አድርገውታል።
በሽር አል አሳድ ከሞስኮ እንዳይወጡ መከልከላቸውንና ሃብታቸው እንዳይንቀሳቀስ ታግዷል መባሉንም አስተባብለዋል።
የሶሪያ እና ብሪታንያ ዜግነት ያላቸው አስማ አል አሳድ ከሩሲያ በመውጣት ወደ ለንደን የመመለስ ፍላጎት እንዳላቸው ሲገለጽ መቆየቱን ዩሮ ኒውስ አስታውሷል።
ይሁን እንጂ የብሪታንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ላሚ በቅርቡ በፓርላማው ንግግር ሲያደርጉ አስማ አል አሳድ ማዕቀብ የተጣለባቸው መሆኑን በመጥቀስ ወደ ሀገሪቱ መግባት እንደማይችሉ ተናግረዋል።
"በስልጣን እስካለሁ ድረስ አንድም የአሳድ የቤተሰብ አባል በብሪታንያ መሸሸጊያ እንዳያገኝ የምችለውን አደርጋለሁ" ማለታቸውም አይዘነጋም።
አስማ አል አሳድ ማን ናቸው?
አስማ አል ከሳድ ከሶሪያውያን ወላጆች በፈረንጆቹ 1975 በእንግሊዝ ነው የተወለዱት።
በምዕራብ ለንደን አክተን ያደጉት አስማ በ25 አመታቸው ወደ ሶሪያ ተመለሱ። ከወራት በኋላም በመኪና አደጋ ህይወታቸው ያለፈ አባታቸውን ስልጣን የተረከቡትን በሽር አል አሳድ አገቡ።
አስማ አል አሳድ ባለፉት 24 አመታት የሶሪያ ቀዳማዊት እመቤት ሆነው በቆዩባቸው አመታት በምዕራባውያን መገናኛ ብዙሃን ስማቸው ተደጋግሞ ይነሳ ነበር።
ለቤተመንግስት ማስዋቢያ ያወጡት የተጋነነ ወጪ፣ 7 ሺ ዶላር የሚያወጣ ጫማ ገዙ መባላቸውና ሌሎች ጉዳዮችም በመገናኛ ብዙሀን እንዲብጠለጠሉ አድርጓቸዋል።
አስማ አል አሳድ የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ ከሀገር እንዲወጡ ሁኔታዎች ቢመቻቹም የትዳር አጋሬን ጥዬ አልወጣም ማለታቸውን በ2016 በሰጡት ቃለምልልስ ተናግረዋል።
በተለያየ ጊዜ እየታመሙ ጭምር ከበሽር አል አሳድ ጎን ያልጠፉት አስማ አል አሳድ የ24 አመት ትዳራቸውን ለመፍታት ሰለማሰባቸው ከሞስኮ በይፋ አልተናገሩም።