በሽር አል አሳድ እንዴት ከሶሪያ ወጡ?
በሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ወቅት የአሳድ ደጋፊ የነበረችው ሩሲያ የሶሪያውን የቀድሞ ፕሬዝዳንት ታድጋቸዋለች ተብሏል

ሞስኮ አል አሳድ ከደማስቆ እንዲወጡ ከመምከር ባሻገር ሚስጢራዊ ጉዞ እንዲያደርጉ ማመችቷም ተገልጿል
ሶሪያን ለ24 አመት የመሩት በሽር አል አሳድ ባለፈው ሳምንት ወደ ሩሲያ ኮብልለዋል።
በሀያት ታህሪር አል ሻም የሚመሩት የታጠቁ ሃይሎች ደማስቆን ሲቆጣጠሩ በአል አሳድ ወንድም ቤት ስር ያገኙት ረጅምና ግዙፍ ዋሻ ያመለጡበት እንደሆነ ቢነገርም እስካሁን ድረስ አወጣጣቸው በግልጽ አልታወቀም።
የአሜሪካው ብሉምበርግ የሩሲያ ምንጮቼ ነገሩኝ ብሎ እንዳስነበበው አማጺያኑ በአንድ ሳምንት ውስጥ አሌፖና ሌሎች ከተሞችን የተቆጣጠሩበት ፍጥነት ሞስኮን አስደንግጧል።
ሩሲያ በሀያት ታህሪር አል ሻም ቡድን ላይ ተደጋጋሚ የአየር ጥቃቶችን በመፈጸም ለአሳድ አጋርነቷን አሳይታለች።
ከኢራን እና ቱርክ ጋርም በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ደረጃ በሶሪያ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ መክራለች።
ይሁን እንጂ ባልተጠበቀ መልኩ ፈጣን ግስጋሴ ላይ የነበሩት የሶሪያ አማጺያን ወደ ደማስቆ ሲቃረቡ በሽር አል አሳድ ከሶሪያ ወጥተው ህይወታቸውን ያተርፉ ዘንድ ምክር ለግሳቸዋለች ነው የተባለው።
የ59 አመቱ በሽር አል አሳድ እና ቤተሰቦቻቸው ከሩሲያ ጋር ጥብቅ ወዳጅነት አላቸው።
አሳድ ጊዜ ሲያዘቀዝቅባቸው ፈጥና የደረሰችውም ሞስኮ ናት ያላል ብሉምበርግ በዘገባው።
በህይወት ያለፈ አባታቸውን ሀፌዝ አል አሳድ መንበር በፈረንጆቹ 2000 የተረከቡት በሽር አል አሳድ ከደማስቆ ወደ ሩሲያ የአየር ማዘዣ በምን መልኩ እንዳመሩ እስካሁን በይፋ አልተገለጸም።
በላታኪያ ግዛት ወደሚገኘው የሩሲያ የጦር መዘዣ እንደደረሱ ግን በፍጥነት በአውሮፕላን ወደ ሩሲያ እንዲጓዙ መደረጉ ተዘግቧል።
ይህን ልዩ ዘመቻም የሩሲያ የደህንነት ባለስልጣናት መርተውታል ነው የተባለው።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሳድ ቤተሰቦች ከ2 ቢሊየን ዶላር በላይ ሀብት እንዳላቸው እንደሚገመት መግለጹ ይታወሳል።
ፋይናንሽያል ታይምስ በቅርቡ ይዞት የወጣው ዘገባ አሳድ አስቀድመው ሀብታቸውን በተለያዩ የባንክ ሂሳቦች፣ በሚስጢራዊ ድርጅቶችና ቤተሰቦቻቸው በኩል ማሸሻቸውን አመላክቷል።
የአሳድ ቤተሰቦች በሞስኮ 40 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ በጥቂቱ 20 አፓርትመንቶችን ገዝተዋል መባሉም በሩሲያ እገዛ ከሞት ያመለጡት የቀድሞው ፕሬዝዳንት የስደት ህይወታቸው የቅንጦት እንደሚሆን አመላክተዋል።