የፈረንሳይ ኦሬንጅ ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ ከመግዛት ሂደት ራሱን አገለለ
የፈረንሳይ ኦሬንጅ ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን 45 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎቱን ገልጾ ነበር
ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ እስካን ማብራሪያ አልሰጡም
የፈረንሳይ ኦሬንጅ ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን 45 በመቶ ድርሻ ከመግዛት ሂደት ራሱን ማግለሉን አስታወቀ።
የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚንስቴር የኢትዮ ቴሌኮምን የ45 በመቶ ድርሻ ለመሸጥ ዓለም አቀፍ ጨረታ ማውጣቱ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎም የፈረንሳዩ ኦሬንጅ እና የተባበሩት አረብ ኢምሬት ቴሌኮም ኩባንያ የሆነው ኢ ኤንድ የተሰኘው ተቋም የኢትዮ ቴሌኮምን የ45 በመቶ ድርሻ ለመግዛት የመወዳደር ፍላጎት እንዳላቸው አሳውቀው ነበር።
- የፈረንሳዩ ኦሬንጅ የቴሌኮሙንኬሽን ኩባንያ የኢትዮ ቴሌኮምን 40 በመቶ ድርሻ ለመግዛት ፍላጎት እንዳው አሳወቀ
- የፈረንሳይና የአረብ ኢምሬት ኩባንያዎች የኢትዮ ቴሌኮምን ድርሻ የመግዛት ፍላጎት እንዳላቸው ተገለፀ
የፈረንሳይ ኦሬንጅ ኩባንያ በትናንትናው እለት ባወጣው መግለጫ የኢትዮ ቴሌኮምን 45 በመቶ ድርሻ ከመግዛት ሂደት ራሱን ለማግለል መወሰኑን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኦሬንጅ ኩባንያ ኢትዮ ቴሌኮምን በከፊል ወደ ግል ለማዞር በሚደረገው የጨረታ ሂደት ላይ ለመሳተፍ ፍለጎት እንዳለው ያሳወቀው በፈረንጆቹ 2021 ነበር።
ኦሬንጅ ከጨረታ ሂደቱ ራሱን ለማግለል የወሰነው ስትራቴጂውን በፍጥነት ለመተግበር አስቻይ ሁኔታ እንደሌል መረዳቱን ተከትሎ እንደሆነም አስታውቋል።
የጨረታ ሂደቱን በበላይነት የሚመሩት ኢትዮ ቴሌኮምና የኢትዮጵያ ፋይናንስ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ እስካን ማብራሪያ አልሰጡም።
ኢትዮ ቴሌኮም በፈረንጆቹ በ2018 የመንግስት ልማት ድርጅቶችን በከፊል ወደ ግል ይዞታ ለማዞር በተያዘው እቅድ ውስጥ ከተካተቱ ድርጅቶች አንዱ ነው።
ኢትዮጵያ ሙሉ ለሙሉ የመንግስት ድርሻ የሆነው ኢትዮ ቴሌኮምን ለመሸጥ ከወሰነች የቆየች ቢሆንም በሰሜን የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተው ጦርነት እንዳዘገየውም ይታወቃል።