ፈረንሳይ የእስራኤልና ሊባኖስን የድንበር ውጥረት የሚያረግብ ምክረሃሳብ አቀረበች
ፓሪስ ያቀረበችው ምክረሃሳብ እስራኤል በሊባኖስ የምትፈጽመውን የአየር ድብደባ እንድታቆምና ሄዝቦላህ ከድንበር 10 ኪሎሜትር እንዲርቅ ይጠይቃል
ሄዝቦላህ እስራኤል በጋዛ የምታካሂደውን ወረራ ካላቆመች ለድርድር አልቀመጥም ብሏል
ፈረንሳይ በእስራኤልና ሊባኖስ ድንበር የተፈጠረውን ውጥረት ያረግባል ያለችውን ምክረሃሳብ ለቤሩት በጽሁፍ ማቅረቧን አስታወቀች።
ሰነዱ ለሊባኖስ ጠቅላይ ሚኒስትር ነጂብ ሚካቲ እና ለሄዝቦላህ አመራሮች መድረሱንም ነው ሬውተርስ የፈረንሳይ ባለስልጣናትን ጠቅሶ የዘገበው።
የጋዛው ጦርነት ወደ ሊባኖስ አድማሱን እንዳያሰፋ ያግዛል የተባለው ምክረሃሳብ በሶስት ምዕራፎች የሚተገበርና ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት የሚደረስበትን ሁኔታ የሚያመላክት ነው።
በመጀመሪያው ምዕራፍ እስራኤልም ሆነች ሄዝቦላህ በድንበር ላይ ግጭት እንዲያቆሙ ይደረጋል።
ግጭት ከቆመ በኋላ በሶስት ቀናት ውስጥ ሄዝቦላህን ጨምሮ የሊባኖስ ጦር ከእስራኤል ድንበር በ10 ኪሎሜትር እንዲርቅ የማድረጉ ተግባርም በሁለተኛው ምዕራፍ ይካሄዳል።
በሶስተኛው ምዕራፍ ደግሞ ሁለቱ ሀገራት አወዛጋቢ የድንበር ጉዳዮችን በተመለከተ በ10 ቀናት ውስጥ ድርድር የሚጀምሩበትን ሁኔታ ያመቻቻሉ ይላል የፈረንሳይ የድርድር ምክረሃሳብ።
የሊባኖስ ጦር በእስራኤል ድንበር አቅራቢያ የገነባቸውን መሰረተልማቶች እንዲያፈርስ የሚጠይቀው የፓሪስ ምክረሃሳብ 15 ሺህ የሀገሪቱ ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ እንዲሰፍርም ይጠይቃል።
ይሁን እንጂ የቤሩት ባለስልጣናት ምክረሃሳቡ የግልጽነት ችግር እንዳለበት በመጥቀስ በቀጣይ ምክክር ይደረግበታል ብለዋል።
ሄዝቦላህ በበኩሉ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን ወረራ እስካላቆመች ድረስ ድርድር አናደርግም ብሏል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ሄዝቦላህ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን ማሳየቱን ተከትሎ የሊባኖስና እስራኤል ድንበር ውጥረት እንዳረበበት ነው።
ሄዝቦላህ እና የእስራኤል ወታደሮች በድንበር አካባቢ በፈጸሙት ጥቃት 200 የሚጠጉ ሊባኖሳውያን እና ከ15 በላይ እስራኤላውያን የተገደሉ ሲሆን፥ በ10 ሺዎች የሚቆጠሩ በድንበር አካባቢ የሚኖሩ ሰዎች ተፈናቅለዋል።
እስራኤልም ሆነች ሄዝቦላህ ወደለየለት ጦርነት መግባት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ቢገልጹም የድንበር ውጥረቱን ለማርገብ የተደረጉ የማሸማገል ጥረቶች እስካሁን አልተሳኩም።
ሄዝቦላህን በሽብርተኝነት የፈረጀችው አሜሪካም እንደ ፈረንሳይ ሁሉ እስራኤልና ሊባኖስን ለማደራደር ጥረት በማድረግ ላይ መሆኗ ይታወቃል።