ፈረንሳይ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያዋን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አደረገች
ከሁለት ቀናት በፊት በሩሲያ ከሞስኮ በቅርብ ርቀት ላይ በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት የዘፈቀደ ጥቃት ከ130 በላይ ሰዎች ተገድለዋል
የፈረንሳይ የሽብር ማስጠንቀቂያዎች ሶስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን አሁን ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የምትለውን አሰምታለች
ፈረንሳይ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያዋን ከፍተኛ ደረጃ ላይ አደረገች።
ፈረንሳይ በሞስኮ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ የሽብር ጥቃት ማስጠንቀቂያዋን ከፍ ማድረጓን ጠቅላይ ሚኒስትር ገብርኤል አታል በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን ያሉት የፈረንሳይ የጸጥታ እና የመከላከያ ባለስልጣናት ከፕሬዝደንት ማክሮን ከመከሩ በኋላ ነው።
የፈረንሳይ የሽብር ማስጠንቀቂያዎች ሶስት ደረጃዎች ያሉት ሲሆን አሁን ከፍተኛ ማስጠንቀቂያ የምትለውን አሰምታለች።
ይህ ማስጠንቀቂያ የፈረንሳይ የጸጥታ አካላት ህዝብ በሚሰበሰብባቸው እንደ ባቡር ጣቢያ እና አየርመንገድ በመሳሰሉ ቦታዎች ቅኝት እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋል።
ከሁለት ቀናት በፊት በሩሲያ ከሞስኮ በቅርብ ርቀት ላይ በተዘጋጀው የሙዚቃ ድግስ ላይ ታጣቂዎች በፈጸሙት የዘፈቀደ ጥቃት ከ130 በላይ ሰዎች ተገድለዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን ጥቃቱን አስመልክተው በሰጡት የመጀመሪያ መግለጫቸው ከዚህ ጥቃት ጀርባ ያሉትን እንደሚያድኑ እና እንደሚቀጡ ዝተዋል።
ለጥቃቱ እስላሚክ ስቴት ኃላፊነቱን እንደሚወስድ ቢገልጽም፣ ፑቲን ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ነበር ካሏቸው አጥቂዎች ጋር ግንኙነት ያለውን ታጣቂ ቡድን ስም በይፋ አልጠቀሱም።
ፑቲን በዩክሬን በኩል መንገድ ከፍተው አጥቂዎቹን ለማስወጣት የሞከሩ ነበሩ ሲሉም ተናግረዋል።
ፕሬዝደንት ፑቲን "አለምአቀፍ ሽብር" ሲሉ በጠሩት በዚህ ጥቃት ዩክሬን ተሳትፎ የለኝም ስትል አስተባብላለች።
ጥቃቱን በማድረስ የተጠረጠሩት ታጣቂዎች በዛሬው እለት ክስ ተመስርቶባቸዋል።