ሩሲያ በሞስኮ ጥቃት ላይ የተሳተፉ አራት ሰዎች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መሰረተች
በሞስኮ በሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 137 ደርሷል
አራቱም ተጠርጣዎች ከፍተኛ ድብደባ የተፈጸመባቸው ሲሆን፤ አንደኛው በዊልቼር ሆኖ ነው ችሎት የቀረበው
ሩሲያ ባሳለፍነው አርብ በሞስኮ በሙዚቃ ኮንሰርት ላይ ጥቃት አድርሰዋል በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር የዋሉ አራት ሰዎ ላይ ክስ መሰረተች።
ባሳለፍነው አርብ በሩሲያዋ ሞስኮ ሲካሄድ በነበረ የሙዚቃ ኮንሰርት ላይ በተፈጸመ ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር 137 መድረሱን እና 100 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው የሩሲያ ባለስልጣናት አስታውቀዋል።
ይህንን ተከትሎም ጥቃቱን አድርሰው ሲሸሹ በቁጥጥር ስር የዋሉ አራት ተጠርጣሪዎች በሞስኮ ፍርድ ቤት መቅረባቸው ነው የተገለጸው።
አራቱም ተጠርጣሪዎች ላይ የሽብርተኝነት ክስ መመስረቱም ነው የተገለጸው።
የሽብርተኝነት ክስ የተከፈተባቸው ተጠርጣዎችም ዳሌርዞን ሚርዞዬቭ፣ ሳይዳክራሚ ሙሮዳሊ ራቻባሊዞዳ፣ ሻምሲዲን ፋሪዱኒ እና መሀመድሶቢር ፋይዞቭ ይባላሉ።
ግለሰቦቹ የታጂኪስታን ዜጎች መሆናቸውን የሩስያ መንግስት የዜና አገልግሎት (ታስ) ዘግቧል።
ተጠርጣሪዎቹ ከፍተኛ ድብደባ እንደደረሰባቸው የተገለጸ ሲሆን፤ አራተኛው ተጠርጣሪ በዊልቼር ላይ ሆኖ ችሎት መቅረቡም ነው የተገለጸው።
በሩሲያ ዋና ከተማ ሞስኮ በተዘጋጀ የሙዚቃ ድግስ ላይ ታጣቂዎች አርብ ምሽት ባደረሱት ድንገተኛ ጥቃት በርካታ ሰዎች ላይ ጉዳት አድርሰዋል።
ታጣቂዎቹ በአውቶማቲክ የጦር መሳሪያ እና በቦምብ ባደረሱት ጥቃት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ137 የደረሰ ሲሆን፤ የቆሰሉ ሰዎች ቁጥር ደግሞ ከ100 መሆኑ ነው የተነገረው።
የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፉ 4 ወንጀለኞች ወደ ዩክሬን ሊያመልጡ ሲሉ በቁጥጥር ስር መዋላቸውንም ፕሬዝዳንት ፑቲን አስታውቀዋል።
“አሁን ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርት እንደሚያመላክተው በዩክሬን በኩል ሽብርተኞች ለማስመለጥ የሚያስችል መንገድ በድንበር በኩል ተዘጋጅቶ እንደነበረ ነው” ብለዋል ፕሬዝዳንቱ።
“ሩሲያ በዚህ የሽብር ጥቃት ላይ የተሳተፉ ሁሉንም አካላት ለይታ ትቀጣለች” ያሉት ፑቲን፤ “ሽብርተኞችን የሚጠብቀው የበቀል እርምጃ ብቻ ነው፤ ከዚህ ውጪ ምንም አማራጭ እና ተስፋ የላቸውም” ብለዋል።