በጥቃቱ የሟቾች ቁጥር ወደ 93 አሻቅቧል
ሩሲያ ትናንት ምሽት ጥቃት ያደረሱ አራቱንም ዋነኛ ተጠርጣሪዎች መያዟን ገለጸች፡፡
በሩሲያ መዲና ሞስኮ ክሮኩስ መዝናኛ ስፍራ ላይ በደረሰ የሽብር ጥቃት እስካሁን የ93 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ ከ100 በላይ ሰዎች ደግሞ ከባድ እና ቀላል ጉዳት ደርሶባቸው ህክምና ላይ ናቸው፡፡
ጥቃቱን አስመልክቶ በወጡ ተንቀሳቃሽ ምስሎች አራት ሰዎች አውቶማቲክ የጦር መሳሪያ በመያዝ በትያትር አዳራሹ ውስጥ ባሉ ሰዎች ላይ ሲተኩሱ ታይተዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ ፖሊስ ከመምጣቱ በፊት ከስፍራው አምልጠው ነበር የተባለ ሲሆን ለዚሁ ተልዕኳቸው በሚል በካሽ በገዟት ተሽከርካሪ ለማምለጥ ሲሞክሩ መያዛቸውን የሩሲያ ብዙሃን መገናኛዎች ዘግበዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በዚህ ተሽከርካሪ ከነ ጦር መሳሪያቸው ከሞስኮ ብዙ ርቀት ላይ ወደ ዩክሬን ድንበር በኩል እንደተያዙም በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
እስካሁንም ከዚህ የሽብር ጥቃት ጋር በተያያዘ 11 ተጠርጣሪዎች በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል የተባለ ሲሆን ተጨማሪ ምርመራዎች በመካሄድ ላይ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
ሩሲያ ወድ ዩክሬን መዲና 31 ሚሳኤሎችን ተኮሰች
ይህ በዚህ አንዳለ እስላሚክ ስቴት የተሰኘው የሽብር ቡድን ለዚህ ጥቃት ሀላፊነት መውሰዱን የገለጸ ሲሆን አሜሪካ በሞስኮ የሽብር ጥቃት ሊደርስ እንደሚችል አስቀድማ አስጠንቅቃም ነበር፡፡
ሩሲያ በበኩሏ የሽብር አደጋው ሊደርስ እንደሚችል መረጃው ከነበራት ተጨማሪ መረጃዎችን ልትነግረን ይገባ ነበር ብላለች፡፡
የአሜሪካ ነጩ ቤተ መንግስት ቃል አቀባይ በበኩላቸው የትናንቱ አደጋ ሊደርስ እንደሚችል መረጃው አልነበረንም ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡