የተከሰሱባቸውን ወንጀሎች የካዱት የቀድሞው ፕሬዝደንት ይግባኝ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል
የቀድሞው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኒኮላስ ሳርኮዚ ዛሬ ሰኞ የካቲት 22 ቀን 2013 ዓ.ም የሙስና ወንጀል መፈጸማቸው በፍርድ ቤት ተረጋግጦ የሦስት ዓመት እስራት ተፈርዶባቸዋል፡፡
የ 66 ዓመቱ ሳርኮዚ እ.ኤ.አ. በ2014 ከፖለቲካ ፓርቲያቸው የምርጫ ዘመቻ ጋር በተያያዘ የቀረበባቸውን ክስ ለማስቀልበስ ጉዳዩን ለያዙት ዳኛ በሞናኮ ትልቅ ስልጣን ለመስጠት መሞከራቸው ነው ጥፋተኛ ያስባላቸው፡፡
በፕሬዝዳንቱ ላይ የሦስት ዓመት የእስር ብያኔ ያሳለፉት ዳኛ ፣ ሳርኮዚ ወደ እስር ቤት ከመሄድ ይልቅ በኤሌክትሮኒክ መለያ አንድ አመት በቤት ውስጥ ሊቆዩ ይችላሉ ብለዋል፡፡ ሁለት ዓመቱ ግን ለሌላ ጊዜ ሊቆያቸው እንደሚችል ተጠቅሷል፡፡ ሳርኮዚ ያለምህረት ጊዜ ተጠቅሶ የእስር ቅጣት የተላለፈባቸው የመጀመሪያው የቀድሞው የፈረንሳይ መሪ እንደሆኑ ዩሮኒውስ ዘግቧል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ 2007 እስከ 2012 ፕሬዝዳንት የነበሩት ሳርኮዚ ባለፈው ዓመት በተካሄደው የ 10 ቀናት የፍርድ ሂደት ላይ የተከሰሱባቸውን ክሶች በሙሉ ክደዋል፡፡ እናም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ይግባኝ ይጠይቃሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ሳርኮዚ በቀጣዩ ወር ደግሞ በ 2012 በተካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ዘመቻ በተጭበረበረ መንገድ ከፍተኛ ወጪ አውጥተዋል በሚል ሌላ ክስ ይጠብቃቸዋል፡፡