መምህር አሰቃይተው ገድለዋል የተባሉ የሱዳን ደህንነቶች ሞት ተፈረደባቸው
በሱዳን 27ቱ የደህንነት ሰዎች የሞት ፍርድ የተፈረደባቸው ህዝባዊ ተቃውሞው ተቀጣጥሎ በነበረበት ወቅት በህግ ቁጥጥር ስር ውሎ የነበረን አንድ መምህር አሰቃይተው በመግደላቸው ነው ተብሏል፡፡
ውሳኔው 30 ለሚጠጋ ዓመታትን ከዘለቀው የኦማር ሃሰን አልበሺር አገዛዝ ለመላቀቅ የሚያስችል መንገድ ለጀመረችው ሱዳን የሚበጅ ትልቅ እርምጃ እየተባለ ይገኛል፡፡
እንደ ሲጂቲ ኤን አፍሪካ ዘገባ ከሆነ ሌሎች 4 የደህንነቱ አባላት በእድሜ ልክ እስራት ሌሎች ተጨማሪ 7 አባላት ደግሞ በነጻ ተለቀዋል፡፡
የደህንነት አባላቱ መምህር አህመድ አል-ከይር ይኖርበት በነበረው በምስራቃዊ ሱዳን ካሳላ ግዛት ይሰሩ እንደነበር ተገልጿል፡፡
በባለፈው ዓመት ወርሃ የካቲት ግድም በደህንነት አባላቱ ቁጥጥር ስር ውሎ የነበረው አህመድ በደረሰበት ከፍተኛ ስቃይና እንግልት ህይወቱ አለፈ መባሉ ተቀስቅሶ የነበረውን ህዝባዊ ተቃውሞ ይበልጥ አቀጣጥሎት የአልበሺርን የስልጣን ዘመን አሳጥሮታል፡፡
በእስር ላይ የሚገኙት አልበሺር በቀረበባቸው የሙስና እና የህገ ወጥ ገንዘብ ይዞታ ክስ 2 አመት እንዲታሰሩ በሃገሪቱ ፍርድ ቤት መወሰኑ የሚታወስ ነው፡፡