ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አዲስ ካቢኔ እንደሚያዋቅሩ ተገልጿል
ፈረንሳይ በታሪኳ ወጣቱን ጠቅላይ ሚኒስትር ልትሾም ነው፡፡
የፈረንሳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ኤልዛቤዝ ቦርን ስልጣናቸውን እንደሚለቁ ማሳወቃቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ካቢኔያቸውን እንደ አዲስ እንደሚያዋቅሩ ተናግረዋል፡፡
ይህን ተከትሎም የ34 ዓመቱ ጋብሪኤል አታል እጩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነዋል፡፡ የሀገሪቱ ፓርላማ ሹመቱን የሚያጸድቅ ከሆነ በፈረንሳይ ታሪክ ወጣቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናሉ ሲል ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
እጩ ጠቅላይ ሚኒስትር አታል የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የቅርብ ሰው እንደሆኑ ይነገርላቸዋል፡፡
አሁን ወደታሰበላቸው ሹመት ከመምጣታቸው በፊት የፈረንሳይ ትምህርት ሚኒስትር ሆነው በማገልገል ላይ ሲሆኑ በተሸሙ በጥቂት ወራት ውስጥ ትምህረት ቤቶች ከየትኛውም ሀይማኖታዊ አልባሳት ነጻ እንዲሆኑ እና በተማሪዎች ስነ ልቦና ማበልጸግ ዙሪያ ስኬታማ ስራ እንደሰሩ ተገልጿል፡፡
በፈረንጆቹ 2016 ላይ የፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፓርቲን የተቀላቀሉት አታል የመንግስት ቃል አቀባይ፣ የበጀት ሚኒስትር እና ሌሎችንም መንግስታዊ ሀላፊነቶችን ላይም ሰርተዋል፡፡
ከፈረንሳይ ዋና ከተማ ፓሪስ ጥቂት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የተወለዱት ጋብሪኤል አታል ሹመቱ ከጸደቀላቸው እስከ 2027 ድረስ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ይቆያሉ ተብሏል፡፡
ፕሬዝዳንት ማክሮን በቀጣዮቹ ቀናት አዲሱን ካቢኔያቸውን ይፋ ደርጋሉ ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን ከጋብርኤል አታል ባለፈ ተጨማሪ አዳዲስ ሚኒስትሮችን እንደሚሾሙ ተገልጿል፡፡