የፈረንሳይ ጦር የሳህል ቀጠና የአይ ኤስ የሽብር ቡድን መሪ መግደሉን ፕሬዝዳንት ማክሮን ገለጹ
ፕሬዝዳንቱ የአል ሳሃራዊ መገደል “የጸረ-ሽብር ትግል ሌላኛው ዋና ስኬት ነው” ብለውታል
አል-ሳሃራዊ በአሜሪካ በጥብቅ የሚፈለግ የጂሃዲስት መሪ መሆኑ ይታወቃል
የፈረንሳይ ጦር በሳህል የመሸገውን የኢስላሚክ ስቴት (አይ.ኤስ) ቡድን መሪ አል-ሳሃራዊን መግደሉን ፕሬዝዳንት ማክሮን ገለጹ።
ከአሜሪካ ወታደሮች እና የፈረንሳይ እርዳታ ሰራተኞች ግድያ ጋር በተያያዘ በአሜሪካ በጥብቅ የሚፈለገው የአይ ኤስ መሪው አቡ ዋሊድ አል ሳሃረዊ የተገደለው የፈረንሳይ ጦር ባደረገው ወታደራዊ ዘመቻ መሆኑን ፐሬዝዳንቱ አስታውቀዋል።
“ይህ በሳህል በምናደርገው የጸረ-ሽብር ትግል ሌላኛው ዋና ስኬት ነው” ሲሉም ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ ገልጸዋል።
የጂሃዲስት መሪው አል ሳሃራዊ እንደፈረንጆቹ 2020 በፈረንሳይ የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች እንደሁም በ2017 በኒጀር በነበሩ የአሜሪካ ወታደሮች ላይ በፈጸመው ጥቃት በጥብቅ ሲፈለግ የቆየ ነው።
በማሊ እና በቡርኪናፋሶ በንጹሃን ላይ ለተፈጸሙ ጥቃቶችም በሰሃራ የመሸገውና በአል ሳሃራዊ የሚመራው ቡዱን ተጠያቂ እንደሆነ ሲነገር ቆይቷል።
አሜሪካ፤ እንደፈረንጆቹ ጥቅምት 4/2017 በአራት የአሜሪካ ልዩ ኃይል አባላትና አራት የኒጀር ወታደሮች ላይ የተፈጸመውን ጥቃት ተከትሎ በወቅቱ የአል-ሳሃራዊ በታላቋ ሰሃራ መኖር መረጃ ላደረሳት አካል 5 ሚልዮን ዶላር መስጠቷ የሚታወስ ነው።
ነሐሴ 9 ቀን 2020 በኒጀር ውስጥ ይሰሩ በነበሩ ስድስት የፈረንሣይ የእርዳታ ሠራተኞች እና ሌሎች ኒጀራውያን ሰራተኞችና ሾፌሮች እንዲገደሉም አል-ሳሃራዊ ትእዛዝ ሰጥቶ ነበር።
አል-ሳሃራዊ ቀደም ሲል የአል-ቃይዳ እንዲሁም እንደፈረንጆቹ 2012 በማሊ የነበሩ የአልጄርያ ዲፕሎማቶችን እና በአልጀርያ የነበሩ የሰፔን የሰብዓዊ እርዳታ ሰራተኞች ያገተው ሙጃ-ኦ የተሰኘው የማሊው አይ ኤስ አባል የነበረ ነው።
ከፈረንጆቹ ከ2013 ወዲህ የፈረንሳይ ጦር በማሊ ባካሄዳቸው ወታደራዊ ዘመቻዎች በርካታ የአይ ኤስ አመራሮች እንደገደለም ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት።
ባለፈው ወርሃ ሰኔ ማክሮን የፀረ-ሽብርተኝነት እንቅስቃሴዎችን ለማጠናከር የአከባቢን ሀይሎች በመደገፍ ቀጠናው ካለፉት ስምንት ዓመታት የበለጠ ለማረጋጋት እንደሚሳራ መግለጻቸው ይታወሳል።