ሩሲያ ለአሜሪካ ልትልከው የነበረውን ኢሜይል በስህተት ወደ ማሊ መላኳ ተገለጸ
የሀገሪቱ መከላከያ ስህተቱ እንዴት ተከሰተ በሚል ምርመራ መጀመሩን ገልጿል
አሜሪካም ከወራት በፊት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሚስጢራዊ መረጃዎችን በስህተት ወደ ማሊ ልካ ነበር
ሩሲያ ለአሜሪካ ልትልከው የነበረውን ኢሜይል በስህተት ወደ ማሊ መላኳ ተገለጸ።
የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር እንዳስታወቀው ወደ አሜሪካ መከላከያ ሊልከው የነበረውን ኢሜይል በስህተት ወደ ማሊ መላኩን አረጋግጫለሁ ብሏል።
ስህተቱ የተፈጠረው በኢሜይል መላኪያ አድራሻ ላይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ሚሊታሪ ተብሎ እየተጻፈ እያለ ማሊ እሚለውን በስህተት በመጫን የተፈጠረ እንደሆነ ሚንስቴሩ በቅድመ ምርመራ ሪፖርቱ ላይ ገልጿል።
ይዩንና በዚህ ወቅት ምን አይነት መረጃዎች በስህተት ወደ ማሊ ተላኩ እሚለውን ጉዳይ ለማወቅ ተጨማሪ ምርመራ እየተደረገ እንደሆነ የሩሲያ መከላከያ ሚንስቴር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።
ቃል አቀባዩ አክለውም ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ስላለው ወታደራዊ ኦፕሬሽኖች የያዘ መረጃ ወደ አፍሪካዊቷ ማሊ ሊላክ እንደሚችል እርግጠኞች ነን ብለዋል።
ሩሲያ እጅግ ወሳኝ መረጃዎቿ በጥብቅ ሊጠበቁ የሚችሉበት ሲስተም ዘርግታለች የአሁኑ ኢሜይል እንደዚህ አይኑት መረጃዎች በስህተት ሊላኩ የሚችሉበት እድል ጠባብ እንደሆነም ተገልጿል።
በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የአሜሪካ ወታደራዊ ኢሜሎች በተመሳሳይ ስህተት ወደ ማሊ መላካቸውን ቢቢሲ ዘግቧል።
የተላከው ወታደራዊ መረጃ ሚስጢራዊ የሆኑ፣ የይለፍ ቃሎች እና የህክምና መረጃዎች እንዳሉበት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።
ማሊ ለምን ከአሜሪካ እና ሩሲያ ወታደራዊ ተቋማት ጋር ስሟ እንደተያያዘ እስካሁን የተባለ ነገር የለም።
ሩሲያ ማሊን ጨምሮ ለስድስት የአፍሪካ ሀገራት በነጻ ለእያንዳንዳቸው 25 ሺህ ቶን ስንዴ እሰጣለሁ ማለቷ ይታወሳል።