በዘንድሮው ኦሎምፒክ ለሚሳተፈው የእስራኤል ልኡክ የ24 ሰአታት የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግለት ታዘዘ
የጋዛን ጦርነት ተከትሎ በተካረረው ውጥረት በአሜሪካ እና አውሮፓ ጸረ ሴማዊነት መጨመሩ ተነግሯል
የጋዛን ጦርነት ተከትሎ በተካረረው ውጥረት በአሜሪካ እና አውሮፓ ጸረ ሴማዊነት መጨመሩ ተነግሯል
በፓሪሱ ኦሎምፒክ ለእስራኤል አትሌቶች የ24 ሰአታት የፖሊስ ጥበቃ እንዲደረግላቸው ታዘዘ፡፡
በሀገሪቱ ፓርላማ የግራ ዘመም ፓርቲ ተመራጮች የእስራኤል አትሌቶች በፓሪሱ ኦሎምፒክ መሳተፍ የለባቸውም በሚል ባሳለፍነው ቅዳሜ ሰላማዊ ሰልፍ መጥራታቸው ይታወሳል።
በሰልፉ ላይ የግራ ዘመም የፓርላማ አባላት የእስራኤል አትሌቶች በፓሪሱ ኦሎምፒክ መሳተፋቸው ተቀባይነት የለውም ብለዋል፡፡
በመጪው አርብ በሚጀመረው የኦሎምፒክ ውድድሮች የእስራኤል ተሳታፊዎች ከፍተኛ ጫና እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል፡፡
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትር በመላው አውሮፓ እየጨመረ የመጣው ጸረ ሴማዊነትን መነሻ በማድረግ ለእስራኤል ተሳታፊዎች በሚንቀሳቀሱበት እና በሚያርፉበት ሆቴል የ24 ሰአታት ጥበቃ ይደረጋል ብሏል፡፡
በእስራኤል እና በሀማስ መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ተከትሎ ጽንፍ የቆሙ ሀሳቦች በሚንጸባረቁበት ምዕራባዊው አለም አትሌቶችን የሚቃወሙ ድምጾች እንዳሉ ሁሉ፤ በተቃራኒው ፍልስጤማውያን እና የፍልስጤም ደጋፊዎች የሚጠሯቸውን ሰልፎች እና የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች የሚቃወሙም አልጠፉም፡፡
ስፖርት እና ፖለቲካ የተለያዩ ናቸው የሚሉ የስፖርት ልኡኩ ያለምንም መሳቀቅ በውድድሩ መሳተፍ መብቱ ሊጠበቅለት እንደሚገባ ሲናገሩ ሌሎች ደግሞ ቴልአቪቭ በጋዛ በፈጸመችው ሰብአዊ ወንጀል በአለም አቀፍ የስፖርት ውድድሮች ላይ መሳተፍ የለባትም እያሉ ይገኛሉ፡፡
ከ52 አመታት በፊት በተካሄደው የሙኒክ ኦሎምፒክ በፍልስጤማውያን ታጣቂዎች በደረሰ ጥቃት 11 የእስራኤል አትሌቶች መገደላቸው ይታወሳል፡፡
ከሰሞኑ በበረከተው ተቃውሞ የተነሳ በፓሪስ መዘጋጃ ቤት አዳራሻ በሙኒክ ኦሎምፒክ የሞቱ የእስራኤል አትሌቶችን ለመዘከር ተዘጋጅቶ የነበረው ፕሮግራም በፈረንሳይ ወደሚገኝው እስራኤል ኢምባሲ ተዘዋውሯል፡፡
እስካሁን ባለው በዘንድሮው ውድድር የሚሳተፉ 15 የሚጠጉ የእስራኤል አትሌቶች የተለያዩ የግድያ ማስፈራርያዎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ደርሷቸዋል፡፡
በዘንድሮው ውድድር 88 አትሌቶች ሀገራቸውን ወክለው ይሳተፋሉ፡፡