ፍልስጤም በፓሪስ ኦሎምፒክ በስምንት አትሌቶች ትወከላለች
የፍልስጤም ኦሎምፒክ ኮሚቴ የፓሪሱን አለማቀፍ መድረክ ፍልስጤማውያን የአይበገሬነት ማሳያ መሆናቸውን እናሳይበታለን ብሏል
በ1996ቱ የአትላንታ ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ፍልስጤም በኦሎምፒክ መድረክ ስምንተኛ ተሳትፎዋን ታደርጋለች
ከስድስት ቀናት በኋላ በሚጀመረው የፓሪስ ኦሎምፒክ ስምንት ፍልስጤማውያን አትሌቶች እንደሚሳተፉ ተገለጸ።
በቶኪዮው ኦሎምፒክ አምስት አትሌቶችን ያሳተፈችው ፍልስጤም ዘጠኝ ወራት በተሻገረው የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ምክንያት ስፖርታዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ ባትችልም ስምንት አትሌቶችን ወደ ፓሪስ ትልካለች ተብሏል።
በ1996ቱ የአትላንታ ኦሎምፒክ ለመጀመሪያ ጊዜ የተሳተፈችው ፍልስጤም በፓሪስ ስምንተኛ የኦሎምፒክ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።
በእስራኤልና ሃማስ ጦርነት 400 የሚጠጉ አትሌቶችና የስፖርት ሰራተኞች ህይወታቸውን አጥተዋል ወይም ቆስለዋል ያለው የፍልስጤም ኦሎምፒክ ኮሚቴ፥ በዚህ ፈታኝ ወቅት በፓሪስ ኦሎምፒክ አትሌቶቻችን መሳተፋቸው አለም አይበገሬነታችን እንዲመለከት ያደርጋል ብሏል።
በጦርነቱ ምክንያት በኦሎምፒክ ለመሳተፍ ሚኒማ ማሟላት ያልቻሉ በርካታ አትሌቶች በመኖራቸው የአለማቀፉ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ለሰባት የፍልስጤም አትሌቶች ልዩ ግብዣ አድርጓል።
የቴኳንዶ አትሌቱ ኦማር ኢስማኤል ብቻ ነው በቻይና ታያን ሚኒማ አሟልቶ በፓሪስ የሚሳተፈው።
ለይላ አል ማስሪ እና ሞሀመድ ደውዳር በ800 ሜትር የሚወዳደሩ ሲሆን፥ የ20 አመቱ ዋሰም አቡ ሳል በኦሎምፒክ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ ፍልስጤምን በቦክስ ውድድር ይወክላል።
ፍልስጤማውያኑ አትሌቶች የመጀመሪያውን የኦሎምፒክ ሜዳልያ ለማጥለቅና የጽናት ተምሳሌትነታቸውን ለማሳየት የፓሪስ ኦሎምፒክ መጀመርን እየተጠባበቁ ነው።
የፍልስጤም የኦሎምፒክ ኮሚቴ ቴክኒካል ዳይሬክተር ናደር ጃዩሲ የኦሎምፒክ ተሳትፎው በራሱ ድል ቢሆንም “እንደሀገር ምን ማድረግ እንደምንችል ለአለም ለማሳየት ተዘጋጅተናል” ብለዋል።
ፍልስጤም በፈረንጆቹ 1995 የአለም ኦሎምፒክ ኮሚቴ አባል መሆኗን የፍራንስ 24 ዘገባ አውስቷል።