ፈረንሳይ ጦሯን ወደ ማሊ ያሰፈረችው ከዘጠኝ ዓመት በፊት ነበር
የፈረንሳይ ጦር ማሊን ሙሉ ለሙሉ ለቆ ወጥቷል።
ፈረንሳይ ከዘጠኝ ዓመት በፊት በምዕራብ እና መካከለኛው አፍሪካ ሀገራት ጽንፈኛ ቡድኖች የሽብር ድርጊቶችን እየፈጸሙ በመሆኑ እና ይሄንን ድርጊት ለማስቆም በሚል ነበር ወደ አካባቢው ጦሯን የላከችው፡፡
ዋና መቀመጫውን ባማኮ ያደረገው የፈረንሳይ ጦር ማሊ፣ቡርኪና ፋሶ፣ኒጀር እና ቻድ ደግሞ ከአምስት ሺህ በላይ የፈረንሳይ ጦር የሰፈረባቸው ሀገራት ናቸው፡፡
በኮለኔል አስሚ ጎይታ የሚመራው የማሊ ወታደራዊ መንግስት ከፈረንሳይ ጋር መልካም ግንኙነት ባለመፍጠሩ ምክንያት ሁለቱ ሀገራት በተደጋጋሚ ግጭቶችን አስተናግደዋል፡፡
ማሊ በባማኮ የነበሩትን የፈረንሳይ አምባሳደርን ከሀገሯ ያባረረች ሲሆን በማሊ የሰፈረው የፈርንሳይ ጦር እንዲወጣም ጠይቃ ነበር፡፡
ይሄንን ተከትሎም ፈረንሳይ በማሊ በሶስት ካምፖች ሰፍሮ የነበረው የፈረንሳይ ጦር በተለያዩ ዙሮች ስታስወጣ የቆየች ሲሆን በዛሬው ዕለት የመጨረሻው ዙር ወታደሮች ከዘጠኝ ዓመት ቆይታ በኋላ ሙሉ ለሙሉ ሀገሪቱን ለቆ ወጥቷል፡፡
በምዕራብ አፍሪካ የተሰማራው የፈረንሳይ ጦር ዋና መቀመጫም ከማሊ ወደ ኒጀር መዛወሩን ፍራንስ 24 ዘግቧል፡፡
በሳህል አካባቢ ሰፍሮ የነበረው የፈረንሳይ ጦር አካባቢውን ለቆ ሲወጣ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገር ሌላ ጦር በአካባቢው ሊሰፍር እንደሚችል ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከዚህ በፊት መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የማሊ ወታደራዊ መንግስት ከተመድ ሰላም አስከባሪዎች ይልቅ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን በማስመጣት አሸባሪዎችን በመዋጋት ላይ እንደሆነ ይነገራል፡፡
ፈረንሳይ እና ሌሎች ምዕራባዊያን ሀገራት ማሊ ከሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር መስራቷ ያበሳጫቸው ሲሆን ከዚህ በፊት በተመድ ስር ከቋቋመው ሰላም አስከባሪ ተልዕኮ ጦራቸውን በማስወጣት ላይ ናቸው፡፡