አረብ ኤምሬትስና ፈረንሳይ በኢነርጂ ዘርፍ ሁሉን አቀፍ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ተፈራረሙ
የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፓሪስ ተወያይተዋል
ስምምነቱ ነዳጅን ጨምሮ የኃይል አማራጮችን በዘላቂነትና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችል ነው
የተባበሩት አረብ ኤምሬትስና ፈረንሳይ በኢነርጂ ዘርፍ ሁሉን አቀፍ የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት መፈራረማቸው ተገለፀ።
የፊርማ ስነ ስርዓቱ የአረብ ኤሚሬትስ ፕሬዝዳንት ሼክ ሞሃመድ ቢን ዛይድ አል ናህያን እና የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በተገኙነት ነው የተካሄደው።
በኃይል ዘርፍ የተደረሰው አጠቃላይ ስትራቴጂካዊ አጋርነት ስምምነት በአረብ ኤምሬትስ እና በፈረንሳይ መካከል የመጀመሪያ ሲሆን፤ በአረብ ኢሚሬትሱ ኤዲኖክ እና በፈረንሳዩ ቶታል ኢነርጂ መካከል ሁለተኛው የስትራቴጂክ አጋርነት ስምምነት ነው።
የመጀመሪያው ስትራቴጂካዊ አጋርነት በአረብ ኤምሬትስ በ2023 ለሚካሄደው 28ኛው የአየር ንብረት ጉባዔ (COP28) ስብሰባ ለመዘጋጀት ውጤታማ የአየር ንብረት ርምጃዎችን ለማስፋት ልምድ ለመለዋወጥ ሲሆን፤ በተጨማሪም የነዳጅን ጨምሮ ኃይል አቅርቦት ደህንነት ለማረጋገጥ እና በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችል ነው።
በአረብ ኢሚሬትስ በኩል ስምምነቱን የፈረሙት ዶ/ር ሱልጣን አህመድ አል ጃበር ፤ "አረብ ኢምሬትስ እንደ አስተማማኝ የሃይል አቅራቢነቷ የኃይል አቅርቦት ደህንነትን ለማረጋገጥ የሚጠበቅባትን እንደመትሰራ አስታውቀዋል
ስምምነቱ አረብ ኤሚሬትስ ለአጋሯ ፈረንሳይ በኃይል ዘርፍ ቀጣይነት ያለው እና ደህንነቱ የተጠበቀ ኃይል በተመጣጣኝ ዋጋ ለማቅረብ የሚያስችል እንዲሁም የሁለቱን ወዳጅ ሀገራት ኢኮኖሚ እድገት እና ብልጽግናን የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ፈረንሳይ እና አረብ ኢሚሬትስ በኢነርጂ ልማት ዘርፍ ረጅም ጊዜ ያስቆጠረ ትብብር የነበራቸው ሲሆን የፈረንሳዩ ቶታል ኢነርጂ በአውሮፓውያኑ ከ1939 ጀምሮ በአቡዳቢ በነዳጅ እና ጋዝ ልማት ዘርፍ ተሰማርቶ እየሰራ ይገኛል።
ከዚህ በተጨማሪም ሁለቱ ሀገራት የተለያዩ የንግድ ግንኙነቶችን ያላቸው ሲሆን፤ በፈረንጆቹ 2020 ብቻ የፈረንሳይ 3.1 ቢሊዮን ዩሮ ዋጋ ያለው ምርት ወደ አረብ ኤሚሬትስ ልካለች፤ በአንጻ ከአረብ ኢሚሬትስ 750 ሚሊዮን ዩሮ ግምት ያለው ምርት ወደ ሀገሯ አስገብታለች።
አረብ ኢሚሬትስ በመካከለኛው ምስራቅ ከሚገኙ ሀገራት ውስጥ በርካታ ቁጥር ያላቸው የፈረንሳይ ኩባንያዎችን ተቀብላ እያስተናገደች ሲሆን፤ በሀገሪቱ የሚገኝ 600 ኩባያዎች ከ30 ሺህ በላይ ሰራተኞችን መቅጠራቸው እና የሚቀጥሩት የሰው ሀይል መጠንም በየአመቱ በ10 በመቶ እድገት እንዳለው መረጃዎች ይጠቁማሉ።