ዩሴይን ቦልት ገንዘቡን ለማስመለስ ወደ ፍርድ ቤት እንደሚያቀና ገልጿል
ታዋቂው ጃማይካዊው የአጭር ርቀት ሻምፒየን አትሌት ዩሴይን ቦልት 12 ሚሊዮን ዶላር ተጭበረበረ።
በኦሎምፒክ ታሪክ ስምንት የወርቅ ሜዳሊያዎችን ያሸነፈው ጃማይካዊው አትሌት ዩሴይን ቦልት ለረጅም ዓመታት የለፋበትን ገንዘብ መጭበርበሩ ተገልጿል።
አትሌቱ መቀመጫውን በጃማይካ መዲና ኪንግስተን ከተማ ባደረገው የደህንነት አክስዮን ኩባንያ ላይ 12 ነጥብ 8 ሚሊዮን ዶላር ድርሻ ነበረው ተብሏል።
ይሁንና ምክንያቱ እስካሁን ባልተገለጸ ሁኔታ አትሌት ቦልት ያለው የአክስዮን ገንዘብ ወደ 12 ሺህ ዶላር ብቻ ሆኖ ተገኝቷል ሲሉ የአትሌቱ ጠበቃ ለሀገሪቱ ብዙሀን መገናኛዎች ተናግረዋል።
ኩባንያው ባሳለፍነው ሳምንት ለዩሴይን ቦልት ገንዘቡ መሰረቁን ካሳወቀ በኋላ ጉዳዩን ወደ ህግ ለመውሰድ ማቀዳቸውንም ጠበቃው ጠቅሰዋል።
የጃማይካ የፋይናንስ ሚንስትር ኒጌል ክላርክ በበኩላቸው በጉዳዩ ዙሪያ ክትትል እና ምርመራ እንደሚያደርጉ አስታውቋል።
ሚንስትሩ አክለውም ከአትሌት ዩሴይን ቦልት በተጨማሪም የሌሎች ግለሰቦች እና ኩባንያዎች ገንዘብ በተመሳሳይ ስለመሰረቁ ሪፖርት እንደተደረገላቸውም ተናግረዋል።
በአጭር ርቀት ለረጅም ጊዜ የነገሰው ዩሴይን ቦልት በፈረንጆቹ 2017 ላይ ራሱን ከውድድር ማግለሉ ይታወሳል።
አትሌት ቦልት ስምንት የኦሎምፒክ የወርቅ ሜዳሊያዎችን ለሀገሩ ጃማይካ ያመጣ ሲሆን የመቶ ሜትር ርቀት ክብረወሰንንም ሰብሯል።