ዛሬ ማለዳ በ'ብስራት ሬድዮ' ከሚተላለፈው 'ከአውቶሞቲቭ የሬድዮ ሾው' ስለፍጥነት መገደቢያ አውርቻለሁ እንጂ የደረሰብኝ አደጋ የለም ብሏል
አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የትራፊክ አደጋ እንዳልደረሰበት ተናገረ።
ታዋቂው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰበት የተለያዩ ሚዲያዎች በመዘገብ ላይ ናቸው።
በአጭር እና ረጅም ርቀት ውድድሮች ላይ ለሀገሩ እና ለራሱ በርካታ ስኬቶችን ያስመዘገበው አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ የትራፊክ አደጋ እንደደረሰበት ተደርጎ የተሰራጨው ዜና ሀሰት መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግሯል።
አትሌቱ እንዳለው "ያለንበት ሁኔታ እጅግ ከባድ ነው፣ ሌላም ነገር ቢሆን እንዲህ ነው የውሸት መረጃ የሚሰራጨው" ሲልም አክሏል።
ዛሬ ጠዋት ላይ በብስራት ሬድዮ ከሚሰራጨው አውቶሞቲቭ የሬድዮ ፕሮግራም ጋር በስልክ ተደውሎልኝ ስለፍጥነት መገደቢያ ወይም ስፒድ ብሬከር ችግር መሆኑን አስተያየት እንደሰጠ አትሌቱ ገልጿል።
"ይህ ማለት ግን ዛሬ በእኔ ላይ የትራፊክ አደጋ ደርሶብኛል ማለት አይደለም" ሲልም አትሌት ሀይሌ ገብረስላሴ ነግሮናል።
በተሰራጨው ሀሰተኛ ዘገባ ምክንያት ቤተሰቦቼ እና ጓደኞቼ አሳስቧቸው እጅግ ብዙ የስልክ ጥሪዎችን እያስተናገደ እንደሆነም አትሌቱ ጠቅሷል።