ፈረንሳይ የወንድ የዘር ፍሬ እጥረት እንደገጠማት ገለጸች
በጎ ፈቃደኛ ወንዶች እና ሴቶች የዘር ፍሬ እና እንቁላል እንዲለግሱ ጥሪ አቅርባለች
በፈረንሳይ ከበጎ ፈቃደኛ ሰዎች በተለገሰ የዘር ፍሬ ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ሰዎች ቁጥር በየዓመቱ እያሻቀበ ነው ተብሏል
ፈረንሳይ የወንድ የዘር ፍሬ እጥረት እንደገጠማት ገለጸች፡፡
የፈረንሳይ ባዮ ሜድሲን ኤጀንሲ እንደገለጸው በሀገሪቱ ያለው የወንድ የዘር ፈውሬ እና የሴት እንቁላል ከፍላጎቱ ጋር የማይጣጣም እንደሆነ አስታውቋል፡፡
እንደ ዩሮ ኒውስ ዘገባ በሀገሪቱ ያለው የዘር ፍሬ እና እንቁላል ለጋሽ በጎ ፈቃደኞች እና ልጅ መውለድ የሚፈልጉ ሰዎች ብዛት የተጣጣመ አይደለም፡፡
ለአብነትም በፈረንጆቹ 2021 ላይ 20 ሺህ ሰዎች ከበጎ ፈቃደኞች በተለገሰ የዘር ፍሬ እና እንቁላል ልጅ ለመውለድ ያመለከቱ ሲሆን ይህ ፍላጎት በ2022 በሁለት ሺህ ጨምሯል ተብሏል፡፡
እንዲሁም በ2023 ይህ አሀዝ በ5 ሺህ ጭማሪ ሲያሳይ በተያዘው ዓመት ደግሞ የበለጠ እየጨመረ እንደሄደ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡
አሁን ላይ በፈረንሳይ ከ7 ሺህ በላይ ሴቶች ልጅ ለመውለድ ከበጎ ፈቃደኞች የተለገሰ የወንድ ዘር ፍሬ ለማግኘት በመጠባበቅ ላይ እንደሆኑ ተገልጿል፡፡
ይሁንና የወንድ የዘር ፍሬ ለመለገስ ፈቃደኛ የሆኑ በጎ ፈቃደኛ ወንዶች ብዛት 676 ብቻ ናቸው የተባለ ሲሆን ፍላጎቱን ለማሟላት 1 ሺህ 400 በጎ ፈቃደኛ ወንዶች ያስፈልጋሉ ተብሏል፡፡
በአንጻሩ ከ26 ሺህ በላይ ሴቶች እንቁላላቸውን ለመለገስ በሂደት ላይ ናቸው የተባለ ሲሆን አብዛኞቹ እድሜያቸው ከ35 ዓመት በላይ የሆናቸው እንደሆኑ ተገልጿል፡፡