በፈረንሳይ የፓርላማ ምርጫ ስደተኛ ጠል ፓርቲዎች አብላጫውን ድምጽ አሸነፉ
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ፓርላማውን በትነው በጠሩት አስቸኳይ ምርጫ ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል
በመጀመሪያ ዙር የፓርላማ ምርጫ ከፍተኛ ድምጽ ያገኙት ቀኝ ዘመም አክራሪ ፓርቲዎች ለሁለተኛው ዙር ምርጫ ብርቱ ቅስቀሳ እያደረጉ ነው
በፈረንሳይ በተካሄደ የፓርላማ ምርጫ ናሽናል ራሊ የተባለው ቀኝ ዘመም ፓርቲ የመጀመርያውን ዙር ድምፅ አንድ ሶስተኛውን በማግኘት እየመራ ነው።
በአክራሪ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ቅኝታቸው የሚታወቁት ዣን ማሪ ለፔን የሚመራው ናሽናል ራሊ ፓርቲ በፈረንሳይ የታችኛው ምክር ቤት ውስጥ አብላጫውን ሊይዝ እንደሚችል እየተነገረ ይገኛል፡፡
በምርጫው ቀኝ ዘመም ፓርቲው ከምክር ቤቱ አጠቃላይ ወንበር 33.2 በመቶ ያሸነፈ ሲሆን፤ ግራ ዘመሙ ጥምር ፓርቲ 28.1 በመቶ ድምጽ ሲያገኝ ለዘብተኛው የማክሮን ስብስብ ደግሞ 21 በመቶ ድምጽ ማግኘቱ ታውቋል።
ይህም ከሁለተኛው የአለም ጦርነት ማብቃት በኋላ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የምክርቤቱን አብላጫ ድምጽ ለመያዝ ሲቃረቡ በታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ ያደርገዋል፡፡
በአውሮፓ ህብረት ፓርላማ ምርጫ ተቀናቃኝ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በብዛት ማሸነፍ ያሳሰባቸው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ፓርላማውን በትነው ያደረጉት አስቸኳይ ምርጫ አደጋ ላይ የጣላቸው ይመስላል፡፡
የናሽናል ራሊ ፓርቲ ወሳኝ የሆኑ የፖሊሲ ጉዳዮችን የማስቀየር አቅምን ይጎናጸፍ ዘንድ 577 መቀመጫዎች ባሉት ምክር ቤት 289 ድምጾችን ማግኝት ይጠበቅበታል፡፡
በህግ እና አስተዳደራዊ ላይ እንዲሁም በስደተኞች ጉዳይ ከማክሮን መንግስት ጋር ሰፊ ልዩነት ያለው ራሊ ፓርቲ በምክር ቤቱ 50 በመቶውን እና ከዛ በላይ ድምጽ የሚያገኝ ከሆነ ቀሪው የማክሮን ሶስት የስልጣን አመታት በፈተና የተሞላ ሊሆን ይችላል፡፡
በሁለተኛው ዙር ምርጫ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች የሚያገኙት ድምጽ እንደመጀመሪያው ዙር ከፍተኛ የሚሆን ከሆነ ፕሬዝዳንት ማክሮን ጠቅላይ ሚንስትራቸውን ከተቀናቃኝ ፓርቲ ለመሾም የሚገደዱ ይሆናል።
በዘንድሮው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ስደተኛ ጠል አክራሪ ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች አብላጫ ድምጽ ማግኘት በቀጠናው በቀጣይ ሊወጡ የሚችሉ ፖሊሲዎች ለስደተኞች ሁኔታዎችን አስቸጋሪ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ይጠበቃል፡፡
በአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ ከፈረንሳዩ በተጨማሪ የግሪክ ፣ፖላንድ ፣ ስፔን ፣ እና ጀርመን ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች ማሸነፍ ችለዋል።
በፈረንሳይ አስቸኳይ ምርጫ አብላጫውን ድምጽ ማግኘት የቻለው የናሽል ራሊ ፓርቲ መሪዋ ማሪን ለ ፔን ባለፉት ሶስት ምርጫዎች ፕሬዝዳንት ለመሆን ተፎካክረው ሳይሳካላቸው ቀርቷል፡፡
ለ ፔን ፈረንሳይ ከአውሮፓ ህብረት እንድትወጣ ሕዝበ ውሳኔ ለማስፈጸም እንዲሁም ወደ ፈረንሳይ የሚገቡ ስደተኞችን ቁጥር መቀነስ የሚያሰችል ፖሊሲ ተግባራዊ አድርጋለሁ በሚል አቋማቸው ይታወቃሉ፡፡