ፈረንሳይ በቴሌግራም መስራች ፓቨል ዱሮቭ ላይ ክስ መሰረተች
ፖሊስ የቴሌግራም ማህበራዊ ትስስር ገጽ የተደራጀ ወንጀልን ለማስኬድ ጥቅም ላይ ውሏል በሚል ምርመራ ጀምሯል
ቅዳሜ እለት በፈረንሳይ በፖሊስ ቁጥጥር ሰር ውሎ የነበረው ፓቨል ፈረንሳይን ለቆ እንዳይወጣ እግድ ተጥሎበታል
ፈረንሳይ በቴሌግራም ማህበራዊ ትስስር ገጽ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓቭል ዱሮቭ ላይ ክስ መሰርታለች፡፡
ከ900 ሚሊየን በላይ ተጠቃሚዎች ያሉት ቴሌግራም የተደራጁ ወንጀሎችን ለማከናውን ውሏል በሚል ፖሊስ ምርመራ እንዲያደርግ የሀገሪቱ ፍርድ ቤት ፈቃድ ሰጥቷል፡፡
ባሰለፍነው ቅዳሜ ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኝ ኤርፖርት በቁጥጥር ስር የዋለው ፓቨል በአምስት ሚሊየን ዮሮ ዋስትና ከተለቀቀ በኋላ ፈረንሳይን ለቆ እንዳይወጣ እግድ ተጥሎበታል፡፡
የፓሪስ አቃቤ ህግ ላውሩ ቤኩዋ ቴሌግራም ህገወጥ ግብይቶችን ለመፈጸም ፣ የእጽ ዝውውር ፣ በማጭበርበር ፣እንዲሁም ለህጻናት ወሲባዊ ጥቃት ጥቅም ላይ ውሏል በሚል ምርመራ እንዲደረግ ከፍርድ ቤት ፈቃድ መገኝቱን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ማህበራዊ ትስስር ገጹ በህገወጥ እንቅስቃሴዎች ዙርያ ምርመራ ለማድረግ በመንግስት አካላት መረጃዎችን እንዲሰጥ በተደጋጋሚ ለቀረበለት ጥያቄ ፈቃደኛ ባለመሆን ተጠያቂ እንዲሆን በምርመራ መዝገቡ ላይ ተካቷል፡፡
በአሁኑ ወቅት የመጀመርያ የክስ ወረቀት የደረሰው ግለሰቡ ምርመራ እንዲረግበት የተዘረዘሩት ጥፋቶች የምርመራ ሂደት አመት እና ከዛ በላይ ሊፈጅ እንደሚችል ነው የተገለጸው፡፡
ለአሁኑ በማህበራዊ ትስስር ገጹ ዋና ስራ አስፈጻሚ ብቻ ወንጀሎቹ በገጹ እንዲፈጸሙ ፈቅዷል በሚል ቢከሰስም በቀጣይ በምርመራ ሂደቱ ተጨማሪ ሰዎች ላይ ክስ ሊመሰረት ይችላል ተብሏል፡፡
የግለሰቡ ጠበቆች ቴሌግራምም ሆነ ዋና ስራ አስፈጻሚው የአውሮፓ ህብረት ህግን አክበረው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸውን ገልጸው የቀረበው ክስ ተገቢ ያልሆነ እና የመናገር ነጻነትን የሚነፍግ ነው ብለዋል፡፡
ፓቭል በፈረንሳይ በቀዳሚነት በቀረበበት የተደራጁ ወንጀለኞች ህገ ወጥ ግብይት እንዲፈጽሙ ፈቅዷል በሚለው ክስ ብቻ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኝ የአስር አመት ፍርድ እና 500 ሺህ ዩሮ ቅጣት ሊጣልበት እንደሚችል ኤፒ ዘግቧል፡፡
ትውልደ ሩስያዊው ፓቭል የፈረንሳይ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትስ ዜጋ ነው፡፡ ይህን ተከትሎም ሩስያ የወንጀል ክሱ ከፖለቲካዊ ፍላጎት የመነጨ ነው በሚል ስትቃወም ዩኤኢ ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተለች እንደምትገኝ አስታውቃለች፡፡
በፈረንጆቹ 2013 የመሰረተው ቴሌግራም በአሁኑ ወቅት ከ950 ሚሊየን በላይ ወርሀዊ ተጠቃሚዎች እንዳሉት ሲነገር፤ በአለም አቀፍ ደረጃ መልእክቶችን ለመቀያየር እና የመዝናኛ እና የመረጃ ይዘቶችን ለማግኝት ተመራጭ እየሆነ መጥቷል፡፡
የ39 አመቱ ቢሊየነር በ2017 የድርጅቱን ዋና ቢሮ ወደ አረብ ኤምሬትሷ ዱባይ ያዛወረ ሲሆን፥ 15 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ሃብት እንዳለው የፎርብስ መረጃ ያሳያል።