የቴሌግራም መተግበሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓቬል ድሮቭ ማን ነው?
ፓቬል ዱሮቭ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቦርጌት አውሮፕላን ማረፊያ ነው በቁጥጥር ስር የዋለው
የ39 አመቱ ትውልደ ሩሲያዊ የፈጠረው ቴሌግራም እንደፌስቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዊቻት ከመሳሰሉት መተግበሪያዎች ጋር መወዳደር ችሏል
የቴሌግራም መተግበሪያ ዋና ስራ አስፈጻሚ ፓቬል ድሮቭ ማን ነው?
ቢሊየነሩ እና የቴሌግራም መልእክት መለዋወጫ መተግበሪያ ባለቤት ፓቬል ዱሮቭ በፈረንሳይ ፓሪስ ከተማ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቦርጌት አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር መዋሉን ሮይተርስ ቲኤፍዋን ቲቪ እና ቢኤፍኤም ቲቪን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደዘገባው በድሮቭ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ትኩረት ያደረገው የቴሌግራም አሰራር የወንጀል ስራዎች እንዳይደረስባቸው እና መከላከል እንዳይቻል የሚያደርግ ነው በሚለው ጉዳይ ነው።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር በዚህ ጉዳይ አስተያየት አልሰጠም።
ሩሲያ ከዚህ በፊት መተግበሪያውን ለማገድ ጥረት አድርጋ የነበረ ቢሆንም አሁን ላይ ዱሮቭ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ እየጣረች መሆኑን ገልጻልች።
ስለድሮቭ እና ቴሌግራም ምን የሚታወቅ ነገር አለ?
የ39 አመቱ ትውልደ ሩሲያዊ የፈጠረው የመልእክት መለዋወጫ መተግበሪያ (ቴሌግራም) እንደፌስ ቡክ፣ ዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዊቻት ከመሳሰሉት የማህበራዊ ሚዲያ መተግበሪያዎች ጋር መወዳደር ችሏል።
ቴሌግሬም በአመት ከአንድ ቢሊዮን በላይ ወርሀዊ ተጠቃሚዎችን ለማፍራት አልሟል።
ቴሌግረም በተለይ በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በቀድሞ የሶቬት ሀገራት ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው።
ቴሌግራም ስለሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኗል፤ የዩክሬን እና የሩሲያ ባለስልጣናት በስፋት ይጠቀሙበታል። አንዳንድ ተንታኞች ቴሌግራም "ቪርቹዋል የጦር ሜዳ" ሆኗል ሲሉም ገልጸውታል።
አጠቃላይ 15.5 ቢሊዮን ዶላር ሀብት እንዳለው የሚገለጸው ዱሮቭ ሩሲያን በ2014 የለቀቀው መንግስት ቪኮንታክቴ ከተባለው እና ቆይቶ ከሸጠው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ የተቃዋሚ ገጾችን እንዲያጠፋ ያቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበለው ከገለጸ በኋላ ነበር።
ዱሮቭ የፈረንሳይ ዜግነት ያገኘው በፈረንጆቹ በነሐሴ 2021 ነበር። ዱሮቭ በ2017 ቴሌግሬምን እና ራሱን ወደ አረብ ኢምሬትስ አዛውሯል። የአረብ ኢምሬትስ ዜግነትም አግኝቷል።
የሚዲያ ሪፖርቶች እንደሚያሳዩት ከሆነ ዱሮቭ ቅዱስ ኪትስ ከተባለችው የካሪቢያን ደሴትም ዜግነት አግኝቷል።
ሩሲያ በ2018 ቴሌግራምን ማገድ የጀመረችው፣ መተግበሪያው ሚስጥራዊ መረጃዎችን ለጸጥታ ኃይሎች በመስጠት እንዲተባበር የቀረበለትን የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ወድቅ ካደረገ በኋላ ነበር። እርምጃው በቴሌግራም ተደራሽነት ላይ የነበረው ተጽዕኖ ውስን የነበረ ቢሆንም በሞስኮ ከፍተኛ ተቃውሞ አስነስቷል።
ቴሌግራም ተወዳጅነቱ እየጨመረ ሲመጣ በአውሮፓ ፈረንሳይን ጨምሮ በበርካታ ሀገራት በደህንነት እና በመረጃ ጥሰት ጉዳይ ጥብቅ ቁጥጥር እያደረጉበት ነው። ባለፈው ግንቦት ወር የአውሮፓ የቴክኖሎጂ ተቆጣጣሪዎች ቴሌግራም ለአውርፓ የኦንላይ የይዘት ቁጥጥር ተገዥ እንዲሆን እየተነጋገሩ መሆኑን አስታውቀው ነበር።
ከማንኛውም አካል ትዕዛዝ ከመቀበል ይልቅ ነጻ መሆኔን እመርጣለሁ" ሲል ነበር ዱሮብ ከሩሲያ ስለመውጣቱ ተጠይቆ የሰጠው ምላሽ።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፓሪስ የሚገኘው ኢምባሲው ስለዱሮቭ ያለውን ሁኔታ እያጣራ እንደሚገኝ ገልጾ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የምዕራባውያን ድርጅቶች እንዲለቀቅ እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርቧል።