የቴሌግራም ማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ቁጥር ወደ አንድ ቢሊየን መጠጋቱ ተነገረ
በሩሲያ የተጀመረው የመልዕክት እና መረጃ መለዋወጫ ገጹ በአጭር ጊዜ ውስጥ በርካታ ተጠቃሚዎችን ማግኝት ችሏል
450 ሚሊየን ሰዎች በቋሚነት በየቀኑ የቴሌግራም ገጽን ይጎበኛሉ
የቴሌግራም ማህበራዊ ትስስር ገጽ ተጠቃሚዎች ወደ አንድ ቢሊየን መጠጋታቸው ተነገረ።
የትስስር ገጹ ወርሀዊ ቋሚ ተጠቃሚዎች ቁጥር 950 ሚሊየን መድረሱን የገጹ መስራች ፓቭል ዱሮቭ ተናግሯል፡፡
የቴሌግራም መስራች እና ባለቤት ትውልደ ሩስያዊው የቴክኖሎጂ ስራ ፈጣሪ ፓቭል ዱሮቭ እንዳስታወቀው በሚያዝያ ወር የገጹ ቋሚ ተጠቃሚ ቁጥር 900 ሚሊየን የነበረ ሲሆን 3 ወራት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ 50 ሚሊየን ተጨማሪ ተጠቃሚዎችን ማግኝት ችሏል፡፡
450 ሚሊየን ሰዎች በየቀኑ ወደ ቴሌግራም ጎራ የሚሉ ሲሆን ገጹ በርካታ ተጠቃሚ ካላቸው እና በብዛት ዳውንሎድ ከሚደረጉ መተግበርያዎች መካከል በስድስተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
በሩሲያ እና ዩክሬን በርካታ ተጠቃሚዎች በመያዝ አገልግሎቱን የጀመረው መተግበርያ በአሁኑ ወቅት በአለም አቀፍ ደረጃ ለመልዕክት መለዋወጫ እና መረጃዎችን ለማግኝት ተመራጭ ከሆኑ ማህበራዊ ትስስር ገጾች መካከል መካተት ችሏል፡፡
ከዋትስአፕ እና ከሌሎች ተመሳሳይ ማህበራዊ ገጾች በሚለየው አሰራሩ ማንኛውም ሰው የራሱን ቻናል መክፈት የተለያዩ መረጃዎችን እንዲሁም ሙዚቃ እና ፊልም የመሳሰሉ የመዝናኛ ይዘቶችን ማሰራጨት ማስቻሉ ተመራጭ እንዳደረገው ይነገራል፡፡
ይሁን እና ከፈጠራ ባለቤቶቹ እውቅና ውጭ የሚሰራጩ ፊልም እና ሙዚቃዎች መጠን መበርከት የቅጅ መብት ባለቤትነትን ይጋፋል በሚል በርካታ የጥበብ ሰዎች በቴሌግራም ላይ ቅሬታ ያቀርባሉ፡፡
የማህበራዊ ትስስር ገጾችን የተጠቃሚ ቁጥር ትንተና ላይ የሚሰራው ዳታ ኤአይ ባወጣው መረጃ መሰረት የትስስር ገጹ በዩክሬን ቀዳሚ የመረጃ እና መልእክት መለዋወጫ መንገድ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ዩክሬን ለብሔራዊ ደህንነት ስጋት ነው በሚል ገጹን በሀገሪቱ ለማገድ እንቅስቃሴ ጀምራለች፡፡
የዩክሬን ኢንተለጄንስ አገልግሎት ተቋም ሩሲያ ቴሌግራምን ሀሰተኛ መረጃዎችን ፣ በኬቭ አስተዳደር ላይ ተቃውሞ የሚያስነሱ ሀሳቦችን እና የጦርነት ፕሮፖጋንዳዎችን እያሰራጨችበት ትገኛለች ሲል ከሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት በርካታ ተጠቃሚ ያላቸው የማህበራዊ ትስስር ገጾችን ደረጃ ፌስቡክ በ3.05 ቢሊየን እየመራ ሲሆን ዋትስአፕ 2.78 ቢሊየን ፣ ዩትዩብ 2.49 ቢሊየን ፣ ኢንስታግራም 2.04 ቢሊየን ተጠቃሚዎች በመያዝ ይከተላሉ፡፡