የቴሌግራም ባለቤት ዱሮቭ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ
በሩሲያ የተወለደው ዱሮብ ከወንድሙ ጋር በመሆን ነበር ቴሌግራምን በፈረንጆቹ 2013 የመሰረተው
በድሮቭ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ትኩረት ያደረገው የቴሌግራም አሰራር የወንጀል ስራዎች እንዳይደረስባቸው የሚያደርግ ነው በሚለው ጉዳይ ነው ተብሏል
የቴሌግራም ባለቤት ዱሮቭ ፈረንሳይ ውስጥ በቁጥጥር ስር ዋለ።
የቴሌግራም መተግበሪያ መስራች እና ዋና ስራ አስፈጻሚ የሆነው የሩሲያ እና ፈረንሳይ ጥምር ዜግነት ያለው ፓቬል ዱሮቭ ከፓሪስ ወጣ ብሎ በሚገኘው ቦርጌት አውሮፕላን ማረፊያ በቁጥጥር ስር ውሏል ተብሏል።
ዱሮቭ በግል ጄቱ ተሳፍሮ እንደነበር እና በፈረንሳይ ለምርመራ ሲፈለግ እንደነበር ሮይተርስ ቲኤፍዋን የተባለውን ቴሌቪዥን ጠቅሶ ዘግቧል።
እንደዘገባው በድሮቭ ላይ እየተካሄደ ያለው ምርመራ ትኩረት ያደረገው የቴሌግራም አሰራር የወንጀል ስራዎች እንዳይደረስባቸው እና መከላከል እንዳይቻል የሚያደርግ ነው በሚለው ጉዳይ ነው።
የፈረንሳይ ሚዲያዎች እንደዘገቡት ከሆነ ዱሮብ ክስ ሊመሰረትበት ይችላል።
የመልእክት መለዋወጫ የሆነው ቴሌግረም በተለይ በሩሲያ፣ በዩክሬን እና በቀድሞ የሶቬት ሀገራት ተጽዕኖ ፈጣሪ ነው። ቴሌግራም አሁን ላይ ከፌስቡክ፣ ከዩቲዩብ፣ ከዋትስአፕ፣ ኢንስታግራም፣ ቲክቶክ እና ዊቻት ቀጥሎ ግዙፍ የማህበራዊ ሚዲያ ነው።
የፈረንሳይ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር በጉዳዩ ላይ አስተያየት አልሰጠም።
በሩሲያ የተወለደው ዱሮብ ከወንድሙ ጋር በመሆን ነበር ቴሌግራምን በፈረንጆቹ 2013 የመሰረተው።ዱሮቭ ሩሲያን በፈረንጆቹ 2014 የለቀቀው መንግስት ቪኮንታክቴ በተባለው እና በሸጠው የማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሉ የተቃዋሚ ገጾችን እንዲዘጋ ያቀረበለትን ጥያቄ እንደማይቀበል ከገለጸ በኋላ ነበር።
"ከማንኛውም አካል ትዕዛዝ ከመቀበል ይልቅ ነጻ መሆኔን እመርጣለሁ" ሲል ነበር ዱሮብ ከሩሲያ ስለመውጣቱ ተጠይቆ የሰጠው ምላሽ።
በፈረንጆቹ የካቲት 2022 ሩሲያ በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ዘመቻ ካወጀች በኋላ ቴሌግራም አልአልፎ ዘግናኝ ምስሎችን እና አሳሳች መረጃዎችን ጨምሮ ያልተገደበ ዋነኛ የመረጃ ምንጭ ሆኖ እያገለገለ ይገኛል።
አንዳንድ ተንታኞች ቴሌግራምን "ቪርቹዋል የጦር ሜዳ" ሲሉ የገለጹት ሲሆን የዩክሬኑ ፕሬዝደንት ዘለንስኪ እና ባለስልጣናቶቻቸው እንዲሁም የሩሲያ መንግስት ይጠቀሙታል።
የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በፓሪስ የሚገኘው ኢምባሲው ስለዱሮቭ ያለውን ሁኔታ እያጣራ እንደሚገኝ ገልጾ፣ መንግስታዊ ያልሆኑ የምዕራባውያን ድርጅቶች እንዲለቀቅ እንዲጠይቁ ጥሪ አቅርቧል።