ማሊ በሀገሯ የሚገኙትን የፈረንሳይ አምባሳደር ለማብራሪያ ጠራች
ማሊ አምባሳደሩን የጠራችው የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በማሊ ጉዳይ አስተያየት መስጠታቸውን ተከትሎ ነው
ማሊ ሽብርተኞችን ለመዋጋት ከሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች ጋር ውይይት መጀመሯ ፈረንሳይን አስቆጥቷል
የፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በማሊ ጉዳይ አስተያየት መስጠታውን ተከትሎ ማሊ በሀገሯ የሚገኙትን የፈረንሳይ አምባሳደር ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠርታለች።
ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ማሊ በጽንፈኛ የሽብር ቡድን አባላት ጥቃት እየተፈተነች ሲሆን፤ ለሀገሪቱ አለመረጋጋትም ዋነኛው መነሻ መሆኑ ይታወሳል።
ማሊ እና ሌሎች የምዕራብ አፍሪካ አገራት በነዚህ የጽንፈኛ የሽብር ቡድን አባላት ጥቃት መጎዳታቸውን ተከትሎ በፈረንሳይ እና አሜሪካ አስተባባሪነት በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ሰላም አስከባሪ ጦራቸውን ወደ ሳህል ቀጠና ልከው ነበር።
ይሁንና የሽብር ቡድኑን ጥቃት ለማስቆም የፈረንሳይ ሰላም አስከባሪ እና የማሊ ጦር በጋራ ወታደራዊ ዘመቻ ለማድረግ የፈረንሳይ መንግስት ፍላጎት እንደሌለው የማሊ የወቅቱ ፕሬዘዳንት ኮለኔል አስሚ ጎይታ ተናግረዋል።
በዚህም ምክንያት የሽብር ጥቃቱን ለማስቆም ማሊ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮችን ወደ ሀገሯ ለማስገባት ውይይት መጀመሯን መግለጹ ይታወሳል።
ይህንን ተከትሎ ፈረንሳይ በዚህ ድርጊት መበሳጨቷን ያስታወቀች ሲሆን፤ እስከዛሬ ለምዕራብ አፍሪካ ያደረገችውን የሰላም ማስከበር ስራ የሚያንኳስስ መሆኑን በፕሬዘዳንቷ በኩል ገልጻለች።
ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የማሊ ድርጊት ተቀባይነት የለውም፤ በመፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጣው ወታደራዊ መንግስት ምርጫ አድርጎ ስልጣን ማስረከብ አለበት ማለታቸው የማሊን መንግስት እንዳላስደስተው ሮይተርስ ዘግቧል።
በዚህም ምክንያት የማሊ መንግስት በሀገሪቱ መዲና ባማኮ የሚገኙትን የፈረንሳይ አምባሳደር ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ባደረጉት ንግግር ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡ ጠይቋል።