ፈረንሳያዊው ጋዜጠኛ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር በማሴር ተጠርጥሮ በኢትዮጵያ መታሰሩን ሲፒጄ ገለጸ
እስሩን የኮነነው ሲፒጄ ጋዜጠኛው በአስቸኳይ እና ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ጠይቋል
ሲፒጄ ጋዜጠኛ አንቶኒ ጋሊንዶ ሲቪል በለበሱ ሰዎች በአዲስ አበባ መያዙን አሳታሚውን ኢንዲጎ ፐብሊኬሽን እና ጠበቃውን ታምሩ ወንድምአገኘሁን አናግሮ ሪፖርት አውጥቷል
ፈረንሳያዊው ጋዜጠኛ ከታጣቂ ቡድኖች ጋር በማሴር ተጠርጥሮ በኢትዮጵያ መታሰሩን ሲፒጄ ገለጸ።
እስሩን የኮነነው ሲፒጄ ጋዜጠኛው በአስቸኳይ እና ያለቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ ጠይቋል።
መቀመጫውን ፈረንሳይ ላደረገው 'አፍሪካ ኢንተሊጀንስ' ለተባለው የግል ጽረ ገጽ የሚሰራው ጋዜጠኛ አንቶኒ ጋሊንዶ ሲቪል በለበሱ ሰዎች በአዲስ አበባ መያዙን ሲፒጄ አሳታሚውን ኢንዲጎ ፐብሊኬሽን እና ጠበቃውን ታምሩ ወንድምአገኘሁን አናግሮ ሪፖርት አውጥቷል።
ሲፒጄ እንደገለጸው ጋዜጠኛው የተያዘው ህጋዊ እውቅና ያለውን የኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባል የሆነውን በቴ ኡርጌሳን በስካይላይት ሆቴል ቃለ መጠይቅ እያደረገ በነበረበት ወቅት ነው።
የሲፒጄ የአፍሪካ ፕሮግራም ኃላፊ አንጀላ ኩይንታል "አንቶኒ ጋሊንዶ ስራውን በመስራቱ የተፈጸመበት መሰረት ቢስ እና ምክንያት የለሽ እስር የሚያናድድ ነው፤ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት በአስቸኳይ ሊለቁት ይገባል"ብለዋል።
ኃላፊዋ የጋሊንዶ እስር በትንሹ ስምንት ጋዜጠኞች ታሰረው በሚገኙባት ኢትዮጵያ ያለውን የፕሬስ ነጻነት አለመከበር የሚያሳይ ተጨማሪ ምሳሌ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ሲፒጄ በሪፖርቱ እንደገለጸው ጋሊንዶ እና በቴ ከተያዙ በኋላ መጀመሪያ በአዲስ አበባ ወደ ቦሌ ሩዋንዳ ፖሊስ ጣቢያ እና ከዚያም ወደ ቦሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ ጣቢያ ተወስደው በአሁኑ ወቅት ታስረው እንደሚገኙ ጠበቃው ለሲፓጄ አሳውቋል።
ጋዜጠኛው ቅዳሜ እለት በቦሌ ፍርድ ቤት መቅረቡን የገለጸው ሲፒጄ መንግስት በሽብር ከፈረጀው እና "ኦነግ ሸኔ" ብሎ ከሚጠራው እና ከመንግስት ጋር ግጭት ውስጥ ከገቡት የፋኖ ታጣቂዎች ጋር በመመሳጠር በአዲስ አበባ ግጭት ለመፍጠር አሲሯል የሚል ክስ ቀርቦበታል ብሏል።
ሲፒጄ እንደገለጸው ጋሊንዶ በዋስ እንዲለቀቅ ተጠይቆ የነበረ ቢሆንም ፓሊስ ተባባሪዎቹን ለመያዝ ሲባል ታስሮ እንዲቆይ መጠየቁን እና ፍርድቤቱም ፓሊስ ሁለቱን ሰዎች እስከ ቀጣይ ቀጥሮ ድረስ አስሮ እንዲያቆያቸው ፈቅዷል።
በፈረንጆች መጋቢት አንድ ጋዜጠኛው እና በቴ ኡርጌሳ በድጋሚ ችሎት ይቀርባሉ።
ሲፒጄ በቅርቡ ባወጣው አመታዋ ሪፖርቱ ኢትዮጵያ ስምንት ጋዜጠኞችን በማሰር ከሰሀራ በታች ካሉ ሀገራት ውስጥ ሁለተኛ የጋዜጠኞች አሳሪ አድርጓታል።