የፈረንሳይ ዋነኛ ተቃዋሚ መሪ ክሬሚያ ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችው በሕዝበ ውሳኔ ስለመሆኑ ዕውቅና ሰጡ
ተፎካካሪዋ ማረን ለፐን ሩሲያ “ኃያል ሀገር ናት” ብለዋል
ማረን ለፐን እና ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ከባድ ፉክክር እያደረጉ ነው ተብሏል
የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ማረን ለፐን ክሬሚያ ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችው “በትክክለኛው” መንገድ መሆኑን ገለጹ፡፡
ፖለቲከኛዋ ከሰሞኑ በሀገሪቱ በሚካሄደው ምርጫ ለፕሬዝዳንትነት እየተወዳደሩ ሲሆን ሩሲያ ሃያል ሀገር እንደሆነች ተናግረዋል፡፡ ክሬሚያ ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችው በግዛቲቱ በተደረገ የሕዝበ ውሳኔ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡
በክሬሚያ በተደረገ ሕዝበ ውሳኔ አብላጫው ሕዝብ ወደ ሩሲያ መቀላቀል እንደሚፈልግ የሩሲያ ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ሲገልጹ ነበር፡፡ ምንም እንኳን ሩሲያ ይህንን ብትልም ምዕራባውያን ግን ሩሲያ “ክሬሚያን አላግባብ ወሰደች” በሚል ሲከሷት ነበር፡፡
ለፈረንሳይ ፕሬዝዳንትነት እየተፎካከሩ ያሉት ቀኝ ዘመሟ ማረን ለፐን ግን ክሬሚያ ወደ ሩሲያ የተቀላቀለችው “ፈቅዳና ወዳ ነው” ብለዋል፡፡ ማረን ለፐን ይህንን አስተያየት ሲሰጡ የመጀመሪያ ምዕራባዊ ፖለቲከኛ ሆነዋል፡፡
የፈረንሳይ ፖለቲከኛ ማረን ለፐን በፈረንጆቹ 2017 ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ተገናኝተው ተወያይተው ነበር፡፡ ማረለን ለፐን ቭላድሚር ፑቲን የሚከተሉት ፖለቲካ እንደሚመቻቸው ገልጸው የነበረ ሲሆን ይህም በርካቶችን ሲያነጋግር እንደነበር ይታወሳል፡፡
ለፈረንሳይ ፕሬዝዳንትነት እየተፎካከሩ ያሉት ማረን ለፐን፤ የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን “አምባገነን” ናቸው ብለው ነበር፡፡ ማረን ለፐን ይህንን አስተያየት የሰነዘሩት ፕሬዝዳንት ማክሮን አስቀድሞ በተፎካካሪያቸው ላይ ትችት ሰንዝረው ስለነበር ነው ተብሏል፡፡
ፈረንሳይ እንደ ኢማኑኤል ማክሮን አይነት “ጽንፈኛ” ፕሬዝዳንት ኖሯት እንደማያውቅም ማረን ለፐን ገልጸዋል፡፡በፈረንሳይ ምርጫ ማረን ለፐን እና ፕሬዝዳንት ማኑኤል ማክሮን ከረር ያለ ፉክክር እያደረጉ ነው ተብሏል፡፡