ማክሮን በ2ኛው ዙር ከቀኝ ዘመም ፓርቲ መሪዋ ሌ ፔን ከፍተኛ ፉክክር እንደሚገጥማቸው ይጠበቃል
በትናንትናው እለት በፈረንሳይ የተካሄደው 12 ተፎካካሪ ፖለቲከኞች የቀረቡበት አንደኛ ዙር ምርጫ፤ ሁለት የመጨረሻ እጩዎች የተለዩበት ሆኖ ተጠናቋል።
በዚህም ቀደም ሲል እንደተገመተው ከ12 ተፎካካሪ ፖለቲከኞች መካከል ማክሮን እና ሌ ፔን ከፍተኛ ድምጽ በማግኘት ወደ ሁለተኛ ዙር ማለፋው ታውቋል።
ሁለቱ እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት እጩ ሆነው ሲቀርቡ ይህ ለሁለተኛ ጊዜያቸው ሲሆን፤ ምርጫው በተለይም ለማሪን ሌ ፔን የፖለቲካ ሕይወት የመጨረሻ ሩጫ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
97 ከመቶ የሚሆነው ቆጠራው ተጠናቋል በተባለው የትናንቱ ምርጫ፤ ከጠቅላላ ድምጽ ሰጪዎች 27 ነጥብ 35 በመቶ የሚሆኑት ለማክሮን፣ 23 ነጥብ 97 በመቶ ለማሪን ሌ ፔን እንዲሁም 21 ነጥብ 7 በመቶ የግራ ዘመም ፓርቲን ለሚመሩት ዣን ሉክ ሚሌቾን ድምጻቸውን ሰጥተዋል።
ከውጤቱ በኋላ፤ በሁለተኛ ዙር ከባድ ፈተና እንደሚገጥማቸው የተረዱት ኢማኑኤል ማክሮን “በፍጹም እንዳትሳሳቱ፣ ምንም እርግጠኛ የተሆነበት ነገር የለም” ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ስሜት የታከለበት ንግግር አድርገዋል።
3ኛ በመሆን ያጠናቀቁትና ወደ ሁለተኛው ዙር ሳያልፉ ቀሩት ዣን ሉክ በበኩላቸው፤ ፈረንሳዊያን በፍጹም ድምጻቸውን ለቀኝ ዘመም መሪዋና ስደተኛ-ጠል ለሆነችው ሌ ፔን መስጠት የለባቸውም ሲሉ መክሯል።
ሌ ፔን እና ማክሮን ከወዲሁ ከፍተኛ የምረጡኝ ቅስቀሳ ውስጥ ገብተዋል፡፡ ላ ፔን ከማክሮን ደጋፊዎች ውጭ ያሉ ፈረንሳዊያን በሙሉ ድምጻቸውን ለሳቸው እንዲሰጡ ተማጽነዋል።
ትንንሽ ድምጽ ያገኙ ፓርቲዎችና ደጋፊዎቻቸው ድጋፋቸውን ለማሪን ሌ ፔን ከሰጡ ማክሮን የማሸነፍ ዕድላቸው አጣብቂኝ ውስጥ ሊገባ እንደሚችል ተገምቷል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በፈረንሳይ ታሪክ በ39 ዓመት የወጣትነት እድሜ የፕሬዝዳንትነትን በትረ ስልጣን የጨበጡና ፈረንሳይን በመምራት ያሉ መሪ ናቸው።