በሩሲያና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት የፈረንሳይ ስለላ ተቋም ኃላፊ ስልጣናቸውን ለቀቁ
ኃላፊው ስልጣናቸውን የለቀቁት የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የማይገመት ነው በሚል ነው
የፈረንሳይ የስለላ ተቋም ስለ ሩሲያና ዩክሬን ጦርነት የተሳሳተ ትንታኔ ሰርቶ ፕሬዝዳንት ማክሮን በተሳሳተ መንገድ እንዲጓዙ አድርጓል
ፈረንሳይ በዩክሬን እና ሩሲያ ጦርነት ላይ ያላት ወታደራዊ ትንተና የተሳሳተ መሆኑን አስታውቃለች።
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦር ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ በሚል ከሩሲያ ጋር ወደ ጦርነት ካመራች 141ኛው ቀን ትገኛለች።
በዚህ ጦርነት ዙሪያ ሊደርሱ ስለሚችሉ ጉዳቶች እና የጦርነቱ ውጤት ምን ሊሆን እንደሚችል የተለያዩ ሀገራት የራሳቸውን ወታደራዊ ትንታኔ አሰቀምጠው አቋም ይይዛሉ።
ፈረንሳይም በራሷ የወታደራዊ ስለላ ተቋም አማካኝነት ትንተና ሰርታ አቋም የያዘች ቢሆንም ስለጦርነቱ የተሰራው ሪፖርት የተሳሳተ እንደሆነ ተገልጿል።
እንደ ፈረንሳይ የዜና ወኪል ኤኤፍፒ ዘገባ የሀገሪቱ ብሄራዊ የስለላ ተቋም ስለ ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት የተሳሳተ ትንታኔ ሰርቶ ፕሬዝዳንት ማክሮን በተሳሳተ መንገድ እንዲጓዙ አድርጓል።
ይሄንን ተከትሎም የሀገሪቱ የወታደራዊ ስለላ ተቋም ኃላፊ ኤሪክ ቪዳውድ ስልጣናቸውን በራሳቸው ፈቃድ ለቀዋል ተብሏል።
የፈረንሳይ መከላከያ የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን የተረዳበት እና ምላሽ እየሰጠ ያለበት አካሄድ ትልቅ ስህተት ያለበት የሚል የትንታኔ ሪፖርት አውጥቷል።
ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ጦርነቱን ተከትሎ ጉዳዩን በዲፕሎማሲ ለመፍታት ከሩሲያ አቻቸው ጋር ወደ ሞስኮ የተጓዙት በዚህ የተሳሳተ ትንታኔ መሰረት እንደሆነም ተገልጿል።
አሜሪካ እና እንግሊዝ ለጉዳዩ የሰጡት ትንታኔ ትክክል እንደነበር በዚህ ሪፖርት ላይ የተገለጸ ሲሆን፤ ፈረንሳይ በዓለም መድረክ ላይ የተሳሳተ መልክ እንዲሰጣትም አድርጓል ተብሏል።
የፈረንሳይ ወታደራዊ የስለላ ተቋም ሩሲያ በኔቶ ላይ ያሳየችው ስጋት ምክንያታዊ መሆኑን እና ዩክሬንን ሙሉ ለሙሉ ላታጠቃ ትችላለች የሚል አቋም መያዙ ተገልጿል።
ይሁንና የአሜሪካ እና ብሪታኒያ የስለላ ተቋማት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ሙሉ ጥቃት እንደምትሰነዝር ከጦርነቱ በፊት አስጠንቅቀው ነበር።
ይህ የፈረንሳይ ወታደራዊ ተቋም ፈረንሳይ ለጦርነት ያላትን ግምት እንድታሳንስ እና ጦርነቱ በፈረንሳዊያን እና ለተቀረው ዓለም ስለሚያስከትለው ጉዳት የተዛባ እይታ እንዲኖራት፣ እንዲሁም ጉዳቱን ለመቀነስ ከአቻ ሀገራት ያነሰ ሚና እንድትጫወት እንዳደረጋት በዘገባው ላይ ተጠቅሷል።