የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ ኦሊቨር ዥሩድ ንብረት ተዘረፈ
ለአሜሪካው ሎስአንጀለስ አግር ኳስ ቡድን የሚጫወተው ዥሩድ ዝርፊያው በፖሊስ እየተመረመረ መሆኑን ክለቡ ገልጿል

ዥሩድ 500 ሺህ ዶላር የሚያወጡ ጌጣጌጦቹ ተዘርፈዋል ተብሏል
የቀድሞው የአርሰናል አጥቂ ኦሊቨር ዥሩድ ንብረት ተዘረፈ፡፡
ፈረንሳዊው የቀድሞው የመድፈኞቹ የፊት መስመር አጥቂ ኦሊቨር ዥሩድ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ዝርፊያ ተፈጽሞበታል ተብሏል፡፡
የታዋቂ ሰዎች ጉዳዮች ዙሪያ ትኩረቱን ያደረገው ቲኤምዜድ የተሰኘው ድረገጽ እንደዘገበው ከሆነ በአሁኑ ወቅት ለአሜሪካው ሎስ አንጀለስ እግር ኳስ ክለብ እየተጫወተ በሚገኘው ዥሩድ ንብረቶች ተዘርፈዋል፡፡
የተጫዋቹ ውድ የእጅ ሰዓቶች እና ጌጣጌጦች ዋነኛ የዝርፊያው ትኩረት ሆነዋል የተባለ ሲሆን የተሰረቁት ንብረቶች ዋጋ 500 ሺህ ዶላር ዋጋ እንዳላቸው ተገልጿል፡፡
ሎስ አንጀለስ አግር ኳስ ክለብ የተጫዋቹን ንብረት ዝርፊያ አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩ በፖሊስ እንደተያዘ እና ከዥሩድ ጎን እንደሚቆም አስታውቋል፡፡
ዝርፊያው ከሁለት ሳምንት በፊት የቤታቸው መስኮት በመስበር ተፈጽሟል የተባለ ሲሆን በተለይም የባለቤቱ ውድ ንብረቶች ኢላማ ተደርገዋል ተብሏል፡፡
የሎስ አንጀለስ ፖሊስ ዝርፊያውን እየመረመረ መሆኑን ገልጾ እስካሁን የተያዙ ተጠርጣሪዎች እንደሌሉ አስታውቋል፡፡
ከሀገሩ ፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አባላት ጋር የ2018 ዓለም ዋንጫ ያሸነፈው ዥሩድ በአርሰናል፣ ቸልሲ፣ ኤሲሚላን መጫወት ችሏል፡፡
በአሜሪካ በታዋቂ ስፖርተኞች ላይ የሚፈጸሙ የተጠኑ ዝርፊያ ወንጀሎች እየጨመሩ እንደመጡ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡