የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ከስጋት የተነሳ የስልክ ቁጥር እና ቀፎ ቀየሩ
ፕሬዝዳንት ማክሮን የእርሳቸውና የሚኒስትሮቻቸው ስልክ እንዳይጠለፍ የሚያደርግ ስብሰባ አድርገዋል
የሞሮኮ ደህንነት ኤጄንሲ የኢማኑኤል ማክሮንን ስልክ ሊጠልፍ ነበር ተብሏል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የስልክ ቁጥር እና የስልክ ቀፎ መቀየራቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።
ማክሮን ስልክ የቀየሩት የሞሮኮ ደህንነት ኤጄንሲ ፔጋሱስ ተብሎ የሚጠራው እስራኤል ሰራሽ የስለላ መሳሪያ ተጠቅሞ ስልካቸውን ሊጠልፈው ይችላል በሚል መሆኑ ተገልጿል።
የፕሬዝዳንት ጽ/ቤት ከፍተኛ ባለስልጣን እንዳሉት ማክሮን ስልክ በቀየሩበት ዕለት በሳይበር ደህንነት ላይ ያተኮረ ስብሰባም መርተው ነበር።
ፕሬዝዳንት ማክሮን የእርሳቸው እና የሚኒስትሮቻቸው ስልክ በስለላ መሳሪያዎች እንዳይጠለፍ የሚያደርግ ስብሰባ ያደረጉ ሲሆን ስልክ ከመቀየርም ባለፈ ፕሬዝዳንቱ ጉዳዩን በከፍተኛ ሁኔታ መያዛቸውን ፍራንስ 24 ዘግቧል።
በዚህም ፕሬዝዳንቱ በሁሉም የግንኙነት መሳሪያዎች ጠንካራ ደህንነት እንደሚስፈልግ ተናግረዋል።
በእስራኤል ኩባንያ የተሰራው ይህ የሥለላ መሳሪያ የፖለቲከኞችን፣ የመብት አራማጆችን እና የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ በመጥለፍ ማወቅ ይፈልጋል በሚል ከሰሞኑ ሲዘገብ ነበር።
የፈረንሳዩ ሌሞንዴ ጋዜጣ የሞሮኮ ደህንነት ኤጄንሲ የማክሮንን እና 15 የፈረንሳይ ባለስልጣናት ስልክ ቁጥር እንዳለውና እ.አ.አ በ 2019 ኢላማ እንዳደረረጋቸው ዘግቧል።
የሞሮኮ መንግስት ግን ይህንን ድርጊት ያወገዘ ሲሆን ይህንን አስወርተዋል ብሎ ባሰባቸው ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።