የሰላም ሚኒስትሯ ሙፈሪያት ካሚል ከጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ የተላከ መልዕክት ለፈረንሳይ ፕሬዝደንት አደረሱ
የሚኒስትሯን ጉብኝት ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለማጥራት እና የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ለማጠናከር ጠቃሚ መሆኑ ተገልጿል
ወ/ሮ ሙፈሪያት ለፈረንሳይ ሴኔት ስለ ኢትዮጵያ ወቅታዊ ጉዳዮች ማብራራታቸውን ውጭ ጉዳይ አስታውቋል
በሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል የተመራ የልዑካን ቡድን ፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለፈረንሳይ ሪፐብሊክ ፕሬዝደንት ኢማኑኤል ማክሮን የላኩትን መልዕክት ማድረሱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገልጿል፡፡
የፕሬዚደንት ማክሮን የአፍሪካ ጉዳዮች ልዩ አማካሪ ሚስተር ፍራንክ ፓሪስ በፕሬዚደንቱ ስም የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ተቀብለዋል፡፡ ፕሬዝደንት ማክሮን በዩኬ በመካሄድ ላይ በሚገኘው እና ትናንት ሰኔ 4 ቀን 2013 ዓ.ም በጀመረው የቡድን 7 ሀገራት ስብሰባ ላይ በመታደም ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡
ሁለቱ ወገኖች ባደረጉት ውይይት ላይ፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ስልጣን ከመጡበት ጊዜ አንስቶ እስካሁን ኢትዮጵያ እያከናወነቻቸው ስላሉ ዘርፈ ብዙ ማሻሻያዎች እና ስለተገኙ ለውጦች ወ/ሮ ሙፈሪያት ገለፃ አድርገዋል ነው የተባለው፡፡
ሚኒስትሯ በተጨማሪም በትግራይ ክልል ስላለው ሁኔታ በዝርዝር ያብራሩ ሲሆን የፌዴራል መንግስት ክልሉን ወደነበረበት ለመመለስ፣ ወንጀለኞችን በቁጥጥር ስር ለማዋል፣ ክልሉን መልሶ ለመገንባት እና በተፈጸሙ ግፎች ዙሪያ ገለልተኛ ምርመራዎች እንዲደረጉ በመደገፍ ልዩ ትኩረት መስጠቱንም አብራርተዋል፡፡
ወ/ሮ ሙፈሪያት በፈረንሳይ ሴኔት ፊት ቀርበው አሁን ያለው የኢትዮጵያ አስተዳደር ሰላማዊና የበለፀገች ሀገር ለመገንባት እየጣለ ስላለው መሠረት ገለጻ ማድረጋቸውንም የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል፡፡ ገለጻቸውን ተከትሎ፣ በኢትዮጵያ ጉዳይ ላይ በሴኔቱ የተደረገው ውይይት ግልጽ ያልሆኑ ጉዳዮችን ለማጥራት እና የሁለቱን ሀገራት ወንድማዊ ግንኙነት ለማጠናከር ጠቃሚ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ጉዳይ አማካሪ አምባሳደር ግርማ ተመስገን እና በፈረንሳይ የኢትዮጵያ አምባሳደር ሄኖክ ተፈራ ሻውል ከወ/ሮ ሙፈሪያት ጋር ወደ ፈረንሳይ ያቀናው ልዑክ አካል ናቸው፡፡
በትግራይ ክልል ካለው ወቅታዊ ሁኔታ እና ከሕዳሴው ግድብ ጋር በተያያዘ በርካታ ጫናዎች እየደረሱበት የሚገኘው የኢትዮጵያ መንግስት፣ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ ለመስጠትና ድጋፎችን ለማሰባሰብ ሰሞኑን መልዕክተኞችን ወደተለያዩ ሀገራት መላክ ጀምሯል፡፡ የውሃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ስለሺ በቀለም ባለፉት ቀናት ወደ ደቡብ ሱዳን፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ በማምራት የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክት ማድረሳቸው አይዘነጋም፡፡