በኢራን ኑክሌር ጉዳይ ስምምነት ለመድረስ "አሁን ላይ ኳሱ በሜዳዋ ውስጥ" ያለው ኢራን ወሳኝ ነች-ኘሬዝደንት ማክሮን
የሚደረሰው ስምምነት ሁሉንም ነገር ባይፈታም እንኳን ስምምነት "ጠቃሚ" ይሆናል ብለዋል
እስራኤል፤ በኢራን የኒውክለር ጉዳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምታቀወም ማስታወቋ ይታወሳል
የኒውክሌር ስምምነት እጣ ፈንታ የሚወሰነው በኢራን ነው ሲሉ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን ተናገሩ፡፡
ለይፋዊ የስራ ጉብኝት በሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር አልጀሪያ የሚገኙት ማክሮን ይህን ያሉት ከአሁን ቀደም (በ2015) ስምምነት ተደርሶበት በነበረው የኢራን የኒውክለር ጉዳይ ላይ በድጋሚ ስምምነት ላይ ለመድረስ እየተደረጉ የሚገኙት ጥረቶች የመሳካት እድላቸው ምን ያክል ነው? በሚል ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሸ ነው፡፡
“አሁን ኳሱ ያለው በኢራን ሜዳ ውስጥ ነው”ም ነው ያሉት ማክሮን፡፡፡
የሚደረሰው ስምምነት ሁሉንም ነገር ባይፈታም እንኳን ስምምነት "ጠቃሚ" ይሆናል ሲሉ መደመጣቸውም ኤኤፍፒ ዘግቧል።
ከአሁን ቀደም ስምምነት ተደርሶበት በነበረው የኢራን የኒውክሌር ጉዳይ ላይ በድጋሚ ስምምነት ላይ ለመድረስ ጥረቶች እየተደረጉ መሆናቸው የሚታወቅ ነው፡፡
አሜሪካ በቀድሞ ፕሬዝዳንቷ ዶናልድ ትራምፕ ትዕዛዝ ከስምምነቱ መውጣቷ ይታወሳል።
ይህን ተከትሎ ጉዳዩ የተቀዛቀዘ ቢመስልም ኢራን ኒውክለር ለመታጠቅ በሚያስችል ደረጃ ከፍተኛ መጠን ያለው ዩራኒየም ማበልጸጓን ቀጥላለች።
ይህን ተከትሎም አውሮፓውያን ወደ ስምምነቱ ለመመለስ የሚመስላቸውን ድርድር በድጋሚ ማካሄድ ጀምረዋል።
ድርድሩ ፈር እየያዘ ነው ቢባልም ግን ከወዲሁ የተለያዩ የተቃውሞ ድምጾች መሰማት ጀምረዋል፡፡
እስራኤል፤ በኢራን የኒውክለር ጉዳይ ስምምነት ላይ ለመድረስ የሚደረጉ ጥረቶችን እንደምታቀወም ከቀናት በፊት ግልጽ አድርጋለች፡፡
የድርድሩ ውጤት እንደማይመለከታትና የድርድሩ አካል እንደማትሆንም በጠቅላይ ሚኒስትሯ በኩል ገልጻለች።
ዬር ላፒድ ቴህራን ኒውክሌር እንዳትታጠቅ ለማድረግ እንደሚሰሩም ተናግረዋል።
ኃያላኑ በድጋሚ ከቴህራን ተደራዳሪዎች ጋር ተገናኝተው ለድርድር ይቀመጣሉ የሚል እምነት እንደሌላቸውም ነው የገለፁት።ያም ሆኖ፤ ፕሬዝዳንት ማክሮንም ኒውክለር እንድትታጠቅ እንደማይፈቅዱና ይህ እንዳይሆን ለማድረግ እንደሚሰሩም ቃል ገብተዋል።