በፈረንሳይ በተነሳው ተቃውሞ ምክንያት የትራንስፖርት አገልግሎቶች እየተቋረጡ ነው
የፈረንሳይ መንግስት የጡረታ ዕድሜን በሁለት ዓመት ለመጨመር የያዘው ማሻሻያ ተቃውሞ ገጥሞታል
የሰራተኛ ማህበራት የስራ ማቆም አድማና ሀገር አቀፍ ሰልፍ ለማድረግ አቅደዋል
የፈረንሳይ የሰራተኛ ማህበራት ከፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የጡረታ ማሻሻያ እቅድ ጋር የሚያደርጉትን ትግል ቀጥለዋል።
በተቃውሞው አብዛኞቹ ባቡሮች መቆማቸውና የነዳጅ አቅርቦት መቋረጡ ተነግሯል።
ትምህርት ቤቶችም ለስድስተኛ ቀን በሀገር አቀፍ ደረጃ አድማ መተዋል ተብሏል።
ለፈረንሳይ መንግስት ጊዜው ወሳኝ መሆኑን የጠቀሰው ሮይተርስ፤ ማሻሻያው በመጋቢት መጨረሻ በፓርላማ ሊጸድቅ ይችላል ብሏል።
የህግ አውጭዎች የጡረታ ዕድሜን በሁለት ዓመት በመጨመር ወደ 64 ዓመት እንዳያሳድጉ ጫና ለማድረግ ማህበራቱ የስራ ማቆም አድማ እንደሚኖር ገልጸዋል።
ይህም ለቀናት ሊቀጥል እንደሚችል ነው ያስታውቁት።
አንድ የሰራተኛ ማህበር ኃላፊ "ማሻሻያው እስኪሰረዝ ድረስ ትግሉ ይቀጥላል" ብለዋል።
የጽዳት ሰራተኞች እና የከባድ መኪና አሽከርካሪዎች የስራ ማቆም አድማውን ተቀላቅለዋል። ይህም ተቃውሞው ወደ ብዙ ዘርፎች እየተዛመተ መሆኑን ማሳያ ተደርጎ ተወስዷል።
ባለፈው ጥር ከ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከተሳተፉበት ተቃውሞ በኋላ በመላው ፈረንሳይ ትልልቅ የተቃውሞ ስልፎችን ለማድረግ መታቀዱ ተገልጿል።