አዲሱ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ፌስቡክንና ትዊተርን የሚገዳደር ነው ተብሏል
የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልደ ትራምፕ አዲስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ይፋ ማድረጋቸውን አስታወቁ፡፡
በትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ ይፋ የተደረገው ይህ አዲስ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ለሁሉም ሰው ድምጽ የሚሰማበት ይሆናል ተብሏል፡፡
ትራምፕ በዚህ ጊዜ እንዳሉት “ታሊባን በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ቢኖርም የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ግን ዝምታን መርጧል፤ ይህ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል፡፡
የቀድሞው ፕሬዘዳንት አክለውም “ይህንን አዲስ ቴክኖሎጂ ይዘን በመምጣታችን ደስተኛ ነኝ ግዙፍ ቴክኖሎጂዎችንን እንገዳደራለን” ሲሉም አክለዋል፡፡ ይሁንና አዲሱ የዶናልድ ትራምፕ ትስስር ገጽ መቼ ስራ እንደሚጀምር አስካሁን አልተገለጸም፡፡
ትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ ከማህበራዊ ትስስር ገጹ በተጨማሪም አማዞንን እና ጎግልን የሚፎካከር ዌብሳይት መክፈቱንም አስታውቋል፡፡
አሜሪካንን ከፈረንጆቹ 2016 እስከ 2020 አመት ድረስ በፕሬዝዳንትነት የመሩት ዶናልድ ትራምፕ ትዊተር ፌስቡክ እና ሌሎች የማህበራዊ ትስስር ገጾችን እንዳይጠቀሙ በኩባናያዎቹ መታገዳቸው ይታወሳል፡፡
እነዚህ ኩባንያዎች የቀድሞውን ፕሬዘዳንት ያገዱት ግጭት ቀስቃሽ ሀሳቦችን ያስተላለፋሉ በሚል ነበር፡፡ በነዚህ ኩባንያዎች እገዳ የተማረሩት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ የተሰኘ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ይፋ አድርገዋል፡፡
ትራምፕ አዲሱን የትስስር ገጽ ይፋ ያደረጉት በቀድሞው የአሜሪካ ኢንቨስትመንት ባንክ ባለሙያ ፓትሪክ ኦርላንዶ ከሚመራው የድጅታል ወርልድ አኩዜሽን ኮርፖሬሽን ጋር በመቀናጀት ነው፡፡
የትራምፕ ሚዲያ እና ቴክኖሎጂ ግሩፕ ለዚህ የማህበራዊ ትስስር ገጽ ማበልጸጊያ ያወጡት ወጪ እስካሁን ያፋ ባይሆንም ኩባንያው 293 ሚሊዮን ዶላር በኦርላንዶ ከሚመራው ኩባንያ እንደሚያቀበል ዘገባው አክሏል፡፡