ቡድን 20 በኒው ዴሊ ጉባኤው የአፍሪካ ህብረትን ቋሚ አባል አድርጎ ተቀበለ
የአባልነት ሀሳቡ ባለፈው ሰኔ ወር በጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ መቅረቡ ይታወሳል
የአፍሪካ ህብረት ከአውሮፓ ህብረት በመቀጠል ቡድን 20ን የተቀላቀለ ሁለተኛው ቀጣናዊ ድርጅት ሆኗል
ቡድን 20 በህንድ ኒው ዴሊ ጉባኤው የአፍሪካ ህብረትን ቋሚ አባል አድርጎ ተቀበለ።
የህንድ ጠቅላይ ሚንስትር ናሬንድራ ሞዲ እንዳስታወቁት የዓለማችን ሀብታም ሀገራትን በአባልነት የያዘው ቡድን 20 የአፍሪካ ህብረትን በቋሚ አባልነት ተቀብሏል።
የ55 ሀገራት ስብስብ የሆነው የአፍሪካ ህብረት የቡድኑ ብቸኛ ሙሉ አባል የሆነው አውሮፓ ህብረት አንድ አይነት አቋም ይኖረዋል።
የአፍሪካ ህብረት ከዚህ ቀደም "ተጋባዥ ዓለም አቀፍ ድርጅት" የሚል ስያሜ ነበረው።
ሞዲ በጉባኤው መክፈቻ ንግግራቸው የህብረቱን ተወካይ የቡድኑ ቋሚ አባላት በሚቀመጡበት ጠረጴዛ እንዲቀመጡ ጋብዘዋል።
"የአፍሪካ ህብረትን በቡድን 20 ቋሚ አባል አድርገን ተቀብለናል። የአፍሪካ ህብረት ቡድን 20ን በመቀላቀሉ የዚህ ዘመን ዓለም አቀፍ ፈተናዎችን ለመፍታት በእጅጉ ይጠቅማል ብለን እናምናለን" ሲል በሮይተርስ የታየው ረቂቅ የውሳኔ ሀሳብ ጠቅሷል።
እርምጃው ባለፈው ሰኔ ወር በጠቅላይ ሚንስትር ሞዲ መቅረቡ ይታወሳል። ቡድን 20 ከዚህ ቀደም 19 ሀገራትንና የአውሮፓ ህብረትን በአባልነት የያዘ ነው።
አባላቱ የዓለምን ጠቅላላ ሀገራዊ ምርት 85 በመቶ፣ የዓለምን የንግድ ልውውጥ 75 በመቶና ሁለት ሦስተኛውን የዓለምን የህዝብ ቁጥር የያዙ ናቸው።