ከትግራይ ክልል ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ሰብዓዊ ድጋፍ ይፈልጋል ተባለ
ከጦርነቱ በኋላ ለ 4.2 ሚሊዮን ዜጎች የሚውል ከ828 ሺ ኩንታል በላይ የድጋፍ እህል መሰራጨቱ ተገልጿል
የተፈናቃዮች ቁጥር መጨመር ችግሩን ሊያባብሰው እንደሚችል የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል
በትግራይ ክልል የተካሔደው ጦርነት ካስከተላቸው መዘዞች መካከል ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ ቀውስ ይገኝበታል፡፡ ጦርነቱን ተከትሎ ሰብዓዊ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ሰዎች ቁጥር በእጅጉ አሻቅቧል፡፡
በአሁኑ ወቅት በክልሉ ከሚገኘው 5.5 ሚሊዮን ህዝብ መካከል 4.5 ሚሊዮኑ ድጋፍ ያስፈልጋቸዋል ተብለው ተለይተዋል፡፡ ይህም በመቶኛ ሲሰላ ከክልሉ ህዝብ ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነው ኑሮውን ለመግፋት እርዳታ ማግኘት ግድ ይለዋል ማለት ነው፡፡
በመቐለ ከተማ ሓወልቲ ትምህርት ቤት ተጠልለው የሚገኙ ተፈናቃዮች ዕለታዊ እርዳታ ከሚጠብቁት መካከል ናቸው፡፡
በትምህርት ቤቱ ቅጥር ጊቢ ወደ አንድ ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የካምፑ ኃላፊ የገለጹ ሲሆን አል ዐይን ኒውስ በስፍራው ተገኝቶ ያናገራቸው ተፈናቃዮች ከምዕራብ ትግራይ ሁመራ እና ወልቃይት አካባቢ ተፈናቅለው መምጣታቸውን ገልጸዋል፡፡
ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት አስተያየት ሰጪዎች ህብረተሰቡ ከሚያደርግላቸው ድጋፍ ውጭ በመንግስት አካል ከአንድ ጊዜ በላይ ድጋፍ እንዳላገኙ ይገልጻሉ፡፡
በአሁኑ ወቅትም የሚፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር እየጨመረ ነው መባሉ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ አሳሳቢ ያደርገዋል፡፡ በመቐለ ከተማ ብቻ በ 8 ትምህርት ቤቶች እና በተለያዩ ግንባታቸው ያልተጠናቀቀ ቤቶች ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ወደ 80 ሺ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መረጃ ያመለክታል፡፡ በአማራ ክልል ተይዞ ከሚገኘው የምዕራብ ትግራይ አካባቢ ደግሞ 700 ሺ ያህል ዜጎች ተፈናቅለው በሽረ ፣ አድዋ ፣ አክሱም ፣ ተምቤን እና ሌሎች አካባቢዎች እንደሚገኙም ነው አስተዳደሩ የገለጸው፡፡
በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በተፈናቃዮች መያዛቸው፣ ከኮሮና ጋር በተያያዘ ተቋርጦ ገና እንደተጀመረ በትግራይ ክልል ዳግም በጦርነቱ ምክንያት የተቋረጠውን ትምህርት ለመጀመር እንቅፋት መሆኑም ተገልጿል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ የፌዴራል መንግስት ለሰብዓዊ ድጋፍ እና ለመሰረተ ልማት ጥገና እስካሁን ከ4 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ማድረጉን የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የጊዜያዊ አስተዳደሩ የህዝብና የመንግስት ግንኙነት ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ እቴነሽ ንጉሴ ለሚዲያ አካላት በሰጡት መግለጫ እንዳሉት ፣ እስከ የካቲት 28 ቀን 2013 ዓ.ም ድረስ ለ 4.2 ሚሊዮን ዜጎች ለመጀመሪያ ዙር የሚውል ከ828 ሺ ኩንታል በላይ የድጋፍ እህል ተሰራጭቷል፡፡
ይሁን እንጂ የምግብ ድጋፍ ስርጭቱ ለተጠቃሚው በአግባቡ እና በፍትሓዊነት እንደማይደርስ አል ዐይን አማርኛ በመቐለ ያነጋገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡ ይህን በተመለከተ አስተያየታቸውን የሰጡት ወ/ሮ እቴነሽ ፣ ከድጋፍ ስርጭቱ ጋር በተያያዘ በርካታ ችግሮች መኖራቸውን አንስተዋል፡፡ ከነዚህም መካከል ስርቆት ፣ የትራንስፖርት እና የፀጥታ ችግር እንዲሁም የተረጂዎች ልየታ በአግባቡ አለመከናወን ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን የትራንስፖርት አቅርቦት እና የፀጥታው ሁኔታ እየተሻሻሉ መምጣታቸውን ጠቅሰው ፣ እስካሁን የተስተዋሉ ጉድለቶችን በመለየት የድጋፍ አቅርቦቱን በተሻለ መልኩ ለማስኬድ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል፡፡
ከምግብ ድጋፍ በተጨማሪ ለተፈናቃዮች የመጠለያ ፣ የፍራሽ ፣ የአልባሳት እና መሰል ድጋፎችም እንደሚያስፈልጉ የገለጹት ወ/ሮ እቴነሽ የዜጎች መፈናቀል ካልቆመ ችግሩ ተወሳስቦ ሊቀጥል እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ሙሉ ነጋ (ዶ/ር) ፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የተፈናቀሉ ዜጎች ክረምት ከመግባቱ በፊት ወደ ቀዬያቸው መመለስ እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ሁኔታው እጅግ አሳሳቢ እንደሚሆን ነው የገለጹት፡፡ ከአማራ ክልል ጋር ያለው አለመግባባት “የህዝቦችን ትስስር በማይጎዳ መልኩ በሰላማዊ መንገድ መፈታት አለበት” ያሉት ዶ/ር ሙሉ ፣ እርሳቸው የሚመሩት ጊዜያዊ አስተዳደር ችግሩን ለመፍታት ከአማራ ክልል ጋር ለመነጋገር ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ዓለማቀፍ የሰብዓዊ ድርጅቶችን በተመለከተ ዶ/ር ሙሉ እንዳሉት ፣ በክልሉ የሰብዓዊ ድርጅቶች ያለገደብ እንዲንቀሳቀሱ መንግስት መፍቀዱን ተከትሎ የተለያዩ ድርጅቶች ወደ ክልሉ በማቅናት ፣ ድጋፍ በሚያደርጉበት ሁኔታ ላይ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር በመነጋገር ላይ ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ ከቀናት በፊት በሰጡት ሳምንታዊ መግለጫ ፣ ለሰብዓዊ ድርጅቶች በክልሉ ገደብ የለሽ እንቅስቃሴ እንዲፈቀድ ሲወተውቱ የነበሩ አካላት ፣ ከተፈቀደ በኋላ ግን ድጋፍ ማቅረብ እንዳልቻሉ ተናግረዋል፡፡ መጀመሪያ እንደነበረው ውትወታ “በእርዳታ የሚያጥለቀልቁን ይመስሉ ነበር” ያሉት ቃል አቀባዩ ነገር ግን ብዙዎቹ ምንም ድጋፍ ሳይይዙ ባዶ እጃቸውን መምጣታቸውን አንስተዋል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በትግራይ ክልል ከተደረገው ሰብዓዊ ድጋፍ 70 በመቶው በኢትዮጵያ መንግስት የቀረበ ሲሆን የተቀረው በለጋሽ ድርጅቶች መቅረቡን መንግስት በተደጋጋሚ መግለጹ ይታወቃል፡፡