ቡድን ሰባት የአሜሪካ፣ጀርመን፣ ብሪታንያ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ካናዳ እና የአውሮፓ ህብረት ጥምረት ነው
የቡድን ሰባት ስብሰባ የዓለም ኢኮኖሚን ከቻይና ጥገኝነት ማላቀቅ በሚል ዋነኛ መወያያ ሆኗል።
የዓለማችን ግዙፍ ኢኮኖሚ ያላቸው ሀገራት ስብስብ የሆነው የቡድን ሰባት ስብሰባ በጃፓን ሒሮሽማ በመካሄድ ላይ ይገኛል ።
በዚህ ስብሰባ ላይ የቡድን ሰባት አባል ሀገራት ፕሬዝዳንቶች እና ጠቅላይ ሚንስትሮች የተሳተፉ ሲሆን የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪም ተገኝተዋል።
የዚህ ጉባኤ ዋነኛ አጀንዳዎችም የዩክሬን ጦር መሳሪያ ጉዳይ፣ በሩሲያ ላይ ተጨማሪ ማዕቀድ መጣል፣ የቻይናን ንግድ መግታት፣ የአርቲፊሺያል ቴክኖሎጂ እና ሌሎችም ይገኙበታል።
መሪዎቹ ዩክሬን ከሩሲያ የሚደርስባትን ወታደራዊ ጥቃት መመከት የሚያስችላትን የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲደረግ ተስማምተዋል።
በተለይም F-16 የተሰኘው የጦር አውሮፕላንን ለዩክሬን ለመስጠት የተስማሙ ሲሆን ብሪታንያ፣ አሜሪካ እና ሌሎችም ሀገራት መስጠት ጀምረዋል።
መሪዎቹ ከቻይና ጋር ያለው ግንኙነት አስጊ ነው ያሉ ሲሆን የቻይናን ንግድ የዓለምን ኢኮኖሚ በማይጎዳ መልኩ መገደብ እንደሚገባ መስማማታቸው ተገልጿል።
የዓለም ኢኮኖሚ በቻይና ላይ የተመሰረተ እንዳይሆን በተናጥል እና በቡድን ጥገኝነትን መቀነስ የሚያስችል እርምጃ እንዲወሰድ መስማማታቸው ተገልጿል።
ከዚህ ጎን ለጎንም ከቻይና ውጪ ከእስያ ሀገራት ጋር ያለውን ግንኙነት ማሻሻል ይገባልም ተብሏል።
ቻይና በእስያ ፓስፊክ ክልል እያደሩገችው ያለው ወታደራዊ መስፋፋት የቡድን ሰባት ሀገራትን አሳስቧል የተባለ ሲሆን በተለይም ታይዋንን ልትወር እንደምትችል ተሰግታል።
የቡድን ሰባት ሀገራት በማጠቃለያ መግለጫቸው ላይ አክለው እንዳሉት የታይዋን እና አካባቢውን ደህንነት ማረጋገጥ ለተቀረው ዓለም አስተማማኝ ሰላም እንዲፈጠር ያደርጋል ብሏል።
ሌላኛው የቡድን ሰባት አባል ሀገራት መወያያ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ሲሆን የቴክኖሎጂ ፈጠራው በተደራጀ እና ተጨማሪ ጉዳት በማያደርስ መንገድ ጥቅም ላይ እንዲውል ከስምምነት ላይ ተደርሷል።
የኑክሌር ጦር መሳሪያ ጠባሳው የምትታወቀው የጃፓኗ ሒሮሽማ ጉባኤን ያስተናገደች ሲሆን ከቡድን ሰባት ሀገራት ጉባኤ ባለፈ ሌሎች ተያያዥ ውይይቶችን እና ምክክሮችን አስተናግዳለች።