"የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ፤ዩክሬንን እናግዛለን" - የቡድን-7 መሪዎች
መሪዎቹ ሩሲያ በክረመንቹክ ከተማ ገበያ ማዕከል ላይ የሰነዘረችው የሚሳኤል ጥቃት “የጦር ወንጀል” ሲሉ ኮንነዋል
ዜሌንስኪ ጥቃቱ በአውሮፓ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል ብለዋል
በጀርመን ጉባኤያቸው እያካሄዱ የሚገኙት የቡድን -7 አባል ሀገራት 'የፈጀውን ጊዜ ይፍጅ፤ ዩክሬንን እናግዛለን 'ሲሉ ተናገሩ።
በጉባኤው በትናንትናው እለት የቪዲዮ መልእክት ያስተላለፉት ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ፤ የቡድን-7 ሀገራት መሪዎች ጦርነቱ ቢያንስ በዓመቱ መጨረሻ እንዲቆም የተቻላቸውን እንዲያደረጉ አልያም ለዩክሬን ተጨማሪ የጦር መሳሪያ ድጋፍ እንዲሰጡ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡
ምእራባውያን እስካሁን በሞስኮ ላይ የወሰዱት እርምጃ በቂ ነው ብለው እንደማያምኑ የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አሁንም ሀገራቱ በሩሲያ ላይ የሚጥሉትን ማዕቀብ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጠይቀዋል፡፡
በዚህም መሰረት የቡድን-7 መሪዎች ባወጡት መግለጫ “የወሰደውን ጊዜ ይፍጅ፤ለዩክሬንን ምናደርገው የፋይናንስ፣ወታደራዊ እና ዲፕሎማሲያዊ እገዛ አጠናክረን እንቀጥልበታለን” ብለዋል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ወደቦች እህል እንዳይወጣ የምታደርገው እገዳ እንድታቆምም ጥሪ ማቅረባቸውም ሮይተርስ ዘግቧል።
በጀርመን ባቫርያ እየተሳለጠ ባለውና በርካታ ቁልፍ ውሳኔዎች ይተላለፉበታል ተብሎ በሚጠበቀው የሃብታም ሀገራት ስብስባ፤ የቡዱኑ አባላት ከሆኑ የካናዳ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ጃፓን፣ ዩናይትድ ኪንግደም እና ኣሜሪካ በተጨማሪ ሁለት የአውሮፓ ህበረት ተወካዮች ተሳታፊዎች ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ የደቡብ አፍሪካ፣ ኢንዶኔዥያ፣ ህንድ እና ሴኔጋል መሪዎች በእንግድነት በጉባኤው በመሳተፍ ላይ ናቸው፡፡
በሌላ ዜና ሩሲያ በዩክሬን ላይ የምትወስደው መጠነ ሰፊ ወታደራዊ እርምጃ አጠናክራ እንደቀጠለችበት ነው፡፡
በትናንትናው እለት በዩክሬኗ ክረመንቹክ ከተማ በሰነዘረችው የሚሳኤል ጥቃት 16 ሰዎች ተገድለዋል።
በጀርመን የተሰበሰቡት የሰባቱ ሀገራት መሪዎች ጥቃቱ ‘የጦር ወንጀል’ ነው በማለት ኮንነዋል።
በዚህ የገበያ ማዕከል የሚሳዔል ጥቃቱ ሲሰነዘር አንድ ሺህ የሚሆኑ ሰዎች በስፍራው ሀገር ሰላም ብለው ሲገበያዩ እንደነበረ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ዜሌንሰኪ ተናግረዋል።
ጥቃቱን ተከትሎ ሰባቱ ሃብታም ሀገራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ንጹሃን ላይ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸም በማያሻማ ሁኔታ ‘የጦር ወንጀል’ ነው በማለት ኮንነዋል።
በጥቃቱ ከሞቱት በተጨማሪ 59 ሰዎች ቆስለዋል።
የሟቾች ቁጥር ከዚህም በላይ ሊሆን እንደሚችል ተፈርቷል።
የገበያ ህንጻው አናት በእሳት ተያይዞ ሲነድ የሚያሳዩ ምስሎች በማህበራዊ የትስስር መድረኮች ሲዘዋወሩ ውለዋል።
ዜሌንስኪ ይህ ጥቃት በአውሮፓ የቅርብ ጊዜ ታሪክ ጭካኔ የተሞላበት የሽብር ታሪክ ሆኖ ይመዘገባል ብለዋል።
ዜሌንስኪ እንዳሉት ይህ የገበያ ስፍራ ለሩሲያ ምንም ዓይነት ወታደራዊ ጠቀሜታ ያለው አይደለም።
“ሩሲያን ያበሳጫት ምናልባት በሰላም ህይወታቸውን ለመምራት የቆረጡ ሰዎች በዚያ ህንጻ መኖራቸው ይሆናል” ሲሉም ተደምጠዋል ዜሌንስኪ።
“ያበዱ አሸባሪዎች ካልሆኑ በስተቀር፣ ምድር ላይ ለህይወት ቦታ የማይሰጡ አሸባሪዎች ካልሆኑ በስተቀር እንዲህ ዓይነት የሚሳኤል ጥቃት በንጹሃን ላይ ማን ይሰነዝራል?’ ሲሉም አክለዋል ፕሬዝዳንቱ።