የቡድን 7 ሀገራት በሩሲያ ላይ ከባድ ቅጣት ለመጣል ቃል ገቡ
ሀገራቱ ባወጡት የጋራ መግለጫ "ሩሲያ ለፍትህ እና ለዘላቂ ሰላም ብቸኛ እንቅፋት ነች" ብለዋል
የቡድን 7 አባል ሀገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት ማዕቀብ በመጣል፣ የውጭ ንግድን በመቆጣጠር እና በሌሎች መንገዶች ከባድ ቅጣት እንደሚያርሱባት ቃል ገብተዋል
የቡድን 7 ሀገራት በሩሲያ ላይ ከባድ ቅጣት ለመጣል ቃል ገቡ።
የቡድን 7 አባል ሀገራት ሩሲያ በዩክሬን ላይ በከፈተችው ጦርነት ምክንያት ማዕቀብ በመጣል፣ የውጭ ንግድን በመቆጣጠር እና በሌሎች መንገዶች ከባድ ቅጣት እንደሚያርሱባት ቃል መግባታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
እንደዘገባው ከሆነ ሀገራቱ ዩክሬንን እስከመጨረሻው እንደሚደግፏትም ገልጸዋል።
ሀገራቱ የዩክሬን-ሩሲያ ጦርነት 1ሺኛ ቀኑን ባስቆጠረበት በትናንትናው እለት ባወጡት የጋራ መግለጫ "ሩሲያ ለፍትህ እና ለዘላቂ ሰላም ብቸኛ እንቅፋት ነች" ብለዋል።
ጣሊያን የ2024ቱ የቡድን 7 አባል ሀገራት ፕሬዝደንት ነች። በዚህ ቡድን ውስጥ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን እና እንግሊዝ ይገኙበታል።
መግለጫው አክሎም "ቡድን 7 ማዕቀብ በመጣል፣ የውጭ ንግዷ ላይ ቁጥጥር በማድረግ እና በሌሎች መንገዶች በሩሲያ ላይ ከባድ ቅጣት ለመጣል ቃል ገብቷል" ብሏል።
ሩሲያ በየካቲት 2022 በዩክሬን ላይ ልዩ ያለችውን ዘመቻ ካወጀች ወዲህ በምዕራቡ አለም እና በሩሲያ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት በ60 አመታት ውስጥ እጅግ ዝቅተኛ የሚባለው ደረጃ ላይ ደርሷል።
ምዕራባውያን ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀብ ከመጣል ባሻገር የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ እያደረጉ ናቸው። ነገርግን ዩክሬን የሩሲያን ኃይሎች ከግዛቷ ማስወጣት አልቻለችም። በተቃራኒው የሩሲያ ኃይሎች ቀስ እያሉ ወደፊት በመግፋት ላይ ይገኛሉ።
ሁለቱ ሀገራት ያስቀመጡት ቅድመ ሁኔታ የተራራቀ በመሆኑ ጦርነቱን በውይይት ለመፍታት የተደረጉ ሙከራዎች እስካሁን አልተሳኩም።