ፖለቲካ
የየመን ታጣቂዎች በእስራኤል ኢሊያት ወደብ "ወሳኝ ኢላማ" ማጥቃታቸውን ገለጹ
ዘመቻው በጋዛ ላይ የተጣለው ማዕቀብ እስከሚነሳ እንደሚቀጥል ቡድኑ ገልጿል
ታጣቂ ቡድኑ ከህዳር 2023 ጀምሮ በአለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ላይ ጥቃት እየሰነዘረ ይገኛል
የየመን ታጣቂዎች በእስራኤል ኢሊያት ወደብ "ወሳኝ ኢላማ" ማጥቃታቸውን ገለጹ።
የየመን ሀውቲ ታጣቂዎች በእስራኤሏ የቀይ ባህር ከተማ ኢሊያት በሚገኝ "ወሳኝ አላማ" ላይ በርካታ ድሮኖችን በመጠቀም ጥቃት ማድረሳቸውን የኢራን የሚደገፈው ቡድን ቃል አቀባይ ያህያ ሳርኤ በትናንትናው እለት ተናግረዋል።
ታጣቂ ቡድኑ ከእስራኤል ጋር እየተዋጋ ላለው ሀማስ አጋርነት ለማሳየት ከህዳር 2023 ጀምሮ በአለም አቀፍ የንግድ መስመሮች ላይ ጥቃት እየሰነዘረ ይገኛል።
"ይህ ዘመቻ ወረራው እስከሚቆም፣በጋዛ ላይ የተጣለው ከበባ እስከሚነሳ እና በሊባኖስ ላይ የተጀመረው ወረራ እስከሚቆም ድረስ ይቀጥላል" ብሏል ሳርኤ በቴሌቪዥን በተላለፈ መልእክቱ።
የሀውቲ ታጣቂዎች ጥቃት የመርከብ ባለቤቶች አቋራጭ የሆነውን የሲውዝ ቦይ እንዳይጠቀሙ በማድረግ አለምአቀፍ ንግዱን ያመሰቃቀለ ሲሆን አሜሪካ እና እንግሊዝ ደግሞ ከየካቲት ጀምሮ የበቀል እርምጃ እንዲወስዱ አነሳስቷቸዋል።
የሀውቲ ታጣቂዎች እስከማዕከላዊ እስራኤል ድረስ በባስቲክ ሚሳይል ጥቃት ፈጽመዋል። እስራኤል ደግሞ በየመኗ ሆዴይዳ ወደብ ላይ የሞት ጉዳት ያስከተለ ከባድ የአየር ጥቃት አድርሰዋል።