24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አትሌት ቢንያም መሐሪና አትሌት አሳየች አይቼው አሸናፊነት ተጠናቀቀ
50 ሺህ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉበት የ2017 ዓ.ም ታላቁ ሩጫ ሩጫ ውድድር ዛሬ ተካዷል
የውድድሩ አሸናፊዎች ከ2500 ሺህ እስከ 100 ሺህ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል
24ኛው ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር በዛሬው እለት ተካሂዷል።
መነሻ እና መድረሻውን መስቀል አደባባይ ባደረገው የዘንድሮ ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ የ10 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድር ላይ 50 ሺህ ሰዎች ተሳትፈዋል።
ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ፣ የአዲስ አባባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሣ፣ የጤና ሚኒስትሯ መቅደስ ዳባና ሌሎችም ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎቸ በውድድሩ ማስጀመሪያ ላይ ተገኝተዋል።
ውድድሩን የወቅቱ የዓለም የሴቶች ማራቶን ሪከርድ ባለቤት ኬኒያዊቷ ሩት ቺፕንግ ኢቴች፣ የኦሎምፒክ የማራቶን ሻምፒዮን አትሌት ታምራት ቶላ እንዲሁም ታዋቂ ኢትዮጵያውያንና ኬንያውያን አትሌቶች በሥፍራው በመገኘት ተከታትለውታል።
በወንዶች በተካሄደው ውድድር የአምናው የውድድሩ አሸናፊ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ቢንያም መሐሪ 1ኛ በመውጣት ያሸነፈ ሲሆን፤ ውድድሩን በተከታታይ በማሸነፍም አዲስ ታሪክ ጽፏል።
በውድድረ አትሌት አዲሱ ነጋሽ 2ኛ ደረጃን በማያዝ ውድድሩን ሲያጠናቅቅ፤ አትሌት ይስማው ድሉ 3ኛ በመውጣት ውድድሩን አጠናቀዋል።
በሴቶች በተካሄደው ውድድር አትሌት አሳየች አይቼው በአንደኝነት ስታጠናቅቅ፣ የኔዋ ንብረት ሁለተኛ እንዲሁም ቦሰና ሙላቴ ሦስተኛ በመሆን ውድድሩን አጠናቀዋል።
ለውድድሩ አሸናፊዎች 250 ሺህ ብር፣ 2ኛ ለወጡት 150 ሺህ ብር እንዲሁም 3ኛ ሆነው ለጨረሱት 100 ሺህ ብር የገንዘብ ሽልማት ተብርክቶላቸዋል።