የቡድን 7 አባል ሀገራት በኔታንያሁ የእስር ማዘዣ ጉዳይ ተመሳሳይ አቋም እንዲይዙ ተጠየቀ
በሚኒስትሮች ደረጃ ለሁለት ቀናት የሚቆይ ጉባኤ እያካሄደ የሚገኝው ቡድን 7 በዛሬው እለት በጉዳዩ ላይ የጋራ አቋም መግለጫ ያወጣል ተብሎ ይጠበቃል
አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በኔታንያሁ ላይ የእስር ማዘዣ ማውጣቱን ተከትሎ ምዕራባውያን በጉዳዩ ላይ የተለያየ ሀሳብ እያንጸባረቁ ነው
የቡድን 7 አባል ሀገራት አለም አቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት በጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ላይ ባወጣው የእስር ማዘዣ ላይ ተመሳሳይ አቋም ሊያንጸባርቁ እንደሚገባ ተነግሯል፡፡
ይህ የተባለው ጣሊያን የዘንድሮውን የአባል ሀገራቱን የሚኒስትሮች ጉባኤ እያካሄደች በምትገኝበት መድረክ ላይ ነው፡፡
በትላንንትናው ዕለት መካሄድ በጀመረው የሚኒስትሮች ጉባኤ የወቅቱ የቡድን 7 ሊቀመንበር የሆነችው ጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ታጃኒ በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ መሆን አለብን ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ ዛሬም ቀጥሎ በሚካሄደው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ጉባኤ መጠናቀቂያ ላይ በሚኖረው የአቋም መግለጫ ላይ ተመሳሳይ አቋም ለማንጸባረቅ እየተወያየን ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የስብስቡ አባል የሆነችው አሜሪካ የፍርድ ቤቱን ውሳኔ መቃወሟ ይታወሳል። የሀገሪቱ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን ሁኔታውን “አሳፋሪ” ሲሉም ገልጸውታል፡፡
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አናሌና ቤርቦክ በበኩላቸው “በእስራኤል እና በሄዝቦላ መካከል በሊባኖስ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ለመድረስ ተስፋዎች እየታዩ ባሉበት ወቅት የጋዛን ጦርነት ሊያስቆሙ የሚችሉ ማናቸውም በጎ ተጽዕኖዎችን ለመተግበር በቡድን 7 እንመክራለን” ብለዋል ።
አይሲሲ ባለፈው ሃሙስ በኔታንያሁ፣የቀድሞው የመከላከያ ሚኒስትር ዮአቭ ጋላንት እንዲሁም በሃማስ መሪ ኢብራሂም አልማስሪ ላይ በጦር ወንጀሎች እና በሰብአዊነት ላይ በሚፈጸም ወንጀል ተሳትፈዋል በሚል የእስር ማዘዣ ማውጣቱ ይታወሳል፡፡
በጉባኤው ላይ የሳኡዲ አረብያ ፣ አረብ ኢምሬትስ ፣ ግብጽ እና ኳታር ተወካዮች በቀረበላቸው ግብዣ በመሳተፍ ላይ ይገኛሉ፡፡
በኔታንያሁ የእስር ማዘዣ ጉዳይ የተቃረነ ሀሳብ እያንጸባረቁ የሚገኙ ሀገራት የሚገኙበት የቡድን 7 ስብስብ ወጥ አቋምን ማንጸባርቅ ሊቸገር እንደሚችል የዘገበው ሮይተርስ፤ በአሁኑ ወቅት ሰፊ ትኩረት ያገኝው የሄዝቦላህ እና እስራኤል የተኩስ አቁም የሚሳካ ከሆነ ሁኔታውን ሊያለዝብው እንደሚችል አስነብቧል፡፡