ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ እየተጠቀመችበት ነው የተባለውን ሚሳይል ማምረቻ ፋብሪካ እያስፋፋች መሆኗ ተነገረ
'ፌብሩዋሪ 11' የተባለው ፋብሪካ የሪዮንግሶንግ ማሼን ኮምፕሌክስ አካል ሲሆን በምስራቅ ጠረፍ በምትገኘው የሰሜን ኳሪያዋ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ሀምሀንግ ውስጥ ይገኛል
ሞስኮና ፒዮንግያንግ፣ ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን እያደካሄደች ባለው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን አሳልፋ ሰጥታለች የሚለውን ክስ አስተባብለዋል
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ እየተጠቀመችበት ነው የተባለውን ሚሳይል ማምረቻ ፋብሪካ እያስፋፋች መሆኗ ተነገረ።
ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን እያካሄደች ባለው ጦርነት ጥቅም ላይ እያዋለችው ነው የባለውን ወሳኝ የሆነውን የአጭር ርቀት ሚሳይል የሚያመርተውን ፋብሪካ እያስፋፋች መሆኑን ሮይተርስ የአሜሪካ አጥኝዎች ቡድንን ጠቅሶ ዘግቧል።
'ፌብሩዋሪ 11' የተባለው ፋብሪካ የሪዮንግሶንግ ማሼን ኮምፕሌክስ አካል ሲሆን በምስራቅ ጠረፍ በምትገኘው የሰሜን ኳሪያዋ ሁለተኛዋ ትልቅ ከተማ ሀምሀንግ ውስጥ ይገኛል።
የዩክሬን ባለስልጣናት በምዕራባውያን ዘንድ ኬኤን-23 ተብለው የሚጠሩት እነዚህ መሳሪያዎች በዩክሬኑ ጦርነት በሩሲያ ጥቅም ላይ ውለዋል።የፋብሪካው መስፋፋት ከዚህ በፊት አልተዘገበም።
ሞስኮና ፒዮንግያንግ፣ ሰሜን ኮሪያ ሩሲያ በዩክሬን እያደካሄደች ባለው ጦርነት ጥቅም ላይ የሚውሉ የጦር መሳሪያዎችን አሳልፋ ሰጥታለች የሚለውን ክስ አስተባብለዋል። ይሁን እንጃ ሩሲያ እና ሰሜን ኮሪያ ባለፈው ሀምሌ ወር ወታደራዊ ስምምነት ተፈራርመዋል።
ከሁለቱ በአንደኛው ላይ ጥቃት በሚቃጣበት ጊዜ አንዳቸው ለሌላኛቸው ሁሉንም አይነት መንገድ ተጠቅመው ወታደራዊ ድጋፍ ለማድረግ የተስማሙትን ስምምነት የሁለቱ ሀገራት መሪዎች ህግ እንዲሆን በቅርቡ መፈረማቸው ይታወሳል።
ሮይተርስ በተመድ የሰሜን ኮሪያ ልኡክ ለማናገር ያደረገው ጥረት አለመሳካቱን ይገልጻል።
'ጀማስ ማርቲን ሴንተር ፎር ነን ፕሮላይፈሬሽን ስተዲስ' የተባለው ቡድን አጥኝዎች እንደሚሉት ከሆነ ባለፈው ጥቅምት ወር የተወሰዱ ምስሎች በፋብሪካ ውስጥ ተጨማሪ የመገጣጠሚያ ህንጻ እየተገነባ መሆኑን ያሳያሉ። ከዚህ በተጨማሪም ምስሎቹ ፒዮንግያንግ በግቢው ውስጥ የመሬት ውስጥ ቦታዎችን መግቢያ እያሳደሰች መሆኑንም ያመለክታሉ ብለዋል አጥኝዎቹ።
እንደመረጃው ከሆነ አዲሱ ህንጻ ሚሳይል ለመገጣጠም ሲያገለግል ከነበረው አሮጌው ህንጻ ከ60-70 በመቶ ይገዝፋል።
በ2023 የሰሜን ኮሪያ መንግስት ሚዲያዎች ኪም ጆንግ ኡን በሀምሀንግ በሚገኘው አዲስ ህንጻ ውስጥ ሲንቀሳቀሱ እና ሰራተኞች ኬኤን-23 ሳይሆን አይቀርም የተባለውን ሚሳይል ሲገጣጥሙ የሚያሳይ ምስል ለቀው ነበር።
ኬኤን-23 የተባለው ሚሳይል ለመጀመሪያ ጊዜ የተሞከረው በ2019 ሲሆን ዝቅ ብሎ በመወንጨፍ የሚሳይል መከላከያ ስርአትን እንዲሸውድ ሆኖ የተሰራ እንደሆነ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ሩሲያ በየካቲት 2022 በዩክሬን ልዩ ያለችው ወታደራዊ ዘመቻ ከከፈተች ወዲህ በሽዎች የሚቆጠሩ ሚሳይሎችን ወደ ዩክሬን አስወንጭፋለች።
ሰሜን ኮሪያ ከሩሲያ ጋር ወታደራዊ ስምምነት ከፈረመች በኋላ የአሜሪካ የኮሪያ ባህረሰላጤ አጋር ከሆነችው ደቡብ ኮሪያ ጋር ከፍተኛ ውጥረት ውስጥ ገብታለች።