የጋቦን መንግስት ገልባጮች ጀነራል ብሪስ ናጉይማን የሀገሪቱ መሪ አድርገው መረጡ
የመፈንቅለ መንግስቱ አቀነባባሪዎች ትናንት ምሽት “የሽግግር ጊዜ መሪ” መርጠናል ብለዋል
ለሶስተኛ የስልጣን ዘመን ተመርጠው የነበሩት ፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ በቁም እስር ላይ ናቸው
በጋቦን የመንግስት ግልበጣ ያደረገው ወታደራዊ ሃይል የሀገሪቱን ጊዜያዊ መሪ መርጧል።
ትናንት ምሽት የተሰበሰቡት የመፈንቅለ መንግስቱ መሪዎች ጀነራል ብሪስ ናጉይማን በሙሉ ድምጽ መምረጣቸውን ነው ያስታወቁት።
ጀነራል ንጉይማ የጋቦን ፕሬዝዳንታዊ ዘብ ሃላፊ እንደነበሩ የተገለጸ ሲሆን መመረጣቸው ከተገለጸ በኋላ በመዲናዋ ሊቨርቢል ከወታደሮች ጋር ደስታቸውን ሲገልጹ ታይቷል።
ጀነራሉ የጋቦን የሽግግር መንግስት መሪ ናቸው ያሉት ወታደራዊ መሪዎቹ፥ የፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎን ወንድ ልጅን በሀገር ክህደት ወንጀል በቁጥጥር ስር አውለነዋል የሚል መግለጫንም አውጥተዋል።
ለሶስተኛ ዙር የስልጣን ዘመን ማሸነፋቸው እንደተነገረ የቁም እስረኛ የሆኑት አሊ ቦንጎ ከቤታቸው በቪዲዮ ባስተላለፉት መልዕክት “አለም ድምጽ ይሁነኝ” ሲሉ ተማጽነዋል።
ወታደራዊ አመራሮቹ ግን ምሽቱን የጋቦንን አዲስ መሪ መርጠዋል፤ የፕሬዝዳንቱ ቀጣይ እጣ ፈንታን በተመለከተ ግን ያሉት ነገር የለም።
የመንግስታቱ ድርጅት፣ የአፍሪካ ህብረት እና ፈረንሳይ መፈንቅለ መንግስቱን የሚቃወም መግለጫ አውጥተዋል።
የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም የጋቦን ወታደራዊ መሪዎች የሲቪል አስተዳደሩን እንዲጠብቅ ነው የጠየቀው።
የአውሮፓ ህብረት እና ብሪታንያም በምዕራብ አፍሪካ እየጨመረ የሄደው የመንግስት ግልበጣ አሳስቢ ስለመሆኑ መግለጻቸውን ሬውተርስ አስነብቧል።
ጋቦን ከአፍሪካ በነዳጅ ሀብቷ አምስተኛዋ ሀገር ስትሆን ማግኒዢየም እና ሌሎች ማዕድናት በስፋት ይገኝባታል።
በ1960 ከፈረንሳይ ነጻ የወጣችው ጋቦን ከአምስት አስርት አመታት በላይ በአሊ ቦንጎ ቤተሰቦች ስትመራ ቆይታለች።
ከቅርብ አመታት ወዲህ የቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛቶች መፈንቅለ መንግስት እየተደጋገመባቸው ነው።
በማሊ፣ ቡርኪናፋሶ፣ ጊኒ፣ ቻድ እና ኒጀር በወታደራዊ ሃይሎች የመንግስት ግልበጣ ተካሂዷል።
ለዚህም በተደጋጋሚ ምክንያት ተደርጎ የሚነሳው የሀገራቱ መሪዎች ከቀድሞ ቅኝ ገዥዋ ፈረንሳይ እና ከምዕራባውያን ጋር በመለጠፍ ሃብታችንን እያስበዘበዙ ነው የሚል ነው።