ፖለቲካ
ክሬሚሊን የዋግነር አመራሮችን የጫነው አውሮፕላን ሆን ተብሎ እንዲከሰከስ ተደርጎ ሊሆን ይችላል አለ
የሩሲያ ምርመራ የቪግኒ ፕሪጎዥኒ ተገድለው ሊሆን እንደሚችል ያመለክታል ተባለ
መንግስት ምርመራው እስኪጠናቀቅ ድረስ መጠበቅ ያስፈልጋል ብሏል
ባለፈው ሳምንት የሩሲያው ዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድንን አዛዥን ጨምሮ 10 ሰዎች ከሞስኮ ወደ ሴንት ፒተርስበርግ ሲጓዙ በአውሮፕላን አደጋ ህይወታቸው አልፏል።
ክሬሚሊን የዋግነር ቅጥረኛ ወታደራዊ ቡድንን መሪ የገደለው የአውሮፕላን አደጋ ሆን ተብሎ የተፈጸመ እንደሆነ እንደሚያጣራ አስታውቋል።
ይህም ይቪግኒ ፕሪጎዥኒ ተገድለው ሊሆን እንደሚችል በሞስኮ በኩል ለመጀመሪያ ጊዜ የቀረበ ይፋዊ ጥርጣሬ ነው።
የክሬምሊን ቃል አቀባይ ዲምትሪ ፔስኮቭ "በምርመራው የተለያዩ እይታዎች ይካተታሉ፤ ሆን ተብሎ ነው የሚለውን ጨምሮ" ብለዋል።
የሩሲያ መንግስት የሚያደርገው ምርመራ እስኪጠናቀቅ ድረስ መጠበቅ እንደሚያስፈልግም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል።
እስካሁን ድረስ የአደጋው መንስኤ የማይታወቅ ሲሆን፤ የአካባቢው ነዋሪዎች ከባድ ፍንዳታ እንደነበርና አውሮፕላኑ እየተምዘገዘገ ሲወድቅ ማየታቸውን ገልጸዋል።
አደጋው ፕሪጎዥኒ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ከተጋጩ ከሁለት ወር በኋላ ደርሷል።
ሞስኮ የብራዚል ስሪት የሆነው አውሮፕላን መከስከስ በዓለም አቀፍ ህግ እንደማትመረምር አስታውቃለች።