ጀነራል ኑጉማ የጋቦን አዲስ መሪ ሆነው ሰኞ ቃለ መሀላ እንደሚፈጽሙ ተነግሯል
የጋቦን አዲስ ወታደራዊ መንግስት ዲሞክራሲን እንደሚመልስ ቃል ገብቷል።
የመንግስት ግልበጣው መሪ ጀነራል ብሪክ ኦሊጉ ኑጉማ የሀገሪቱ ዲሞክራሲ ተሻሽሎ እንደሚመልስና መስተጓጎሉም ጊዜያዊ መሆኑን ገልጸዋል።
ሆኖም የሀገሪቱ ተቃዋሚዎች ጥምረት ወታደራዊ መንግስቱ ስልጣን ለህዝባዊ መንግስት ለማስረከብ ምልክት እያሳየ አይደለም ሲሉ ወቅሷል።
አርብ በቴሌቪዥን መስኮት የቀረቡት ጀነራሉ መንግስታቸው በፍጥነት እንደሚሰራ ገልጸው፤ ነገር ግን አንድ አይነት ሰዎችን ስልጣን ላይ ያቆየ ምርጫ በማድረግ ተመሳሳይ ስህተት እንደማይሰሩ ተናግረዋል።
ከሰሞኑን የተካሄደው ምርጫ ትክክለኛ አሸናፊ ነኝ የሚለው ተቃዋሚ ጥምረት፤ በጋቦን ህዝባዊ አስተዳደር እንዲመለስ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እንዲወተውት ጥሪ አቅርቧል።
ጀነራል ብሪክ ኦሊጉ ኑጉማ የጋቦን አዲስ መሪ ሆነው ሰኞ ቃለ መሀላ እንደሚፈጽሙ ተነግሯል።
ፕሬዝዳንት አሊ ቦን የቤት ውስጥ እስረኛ መደረጋቸውም ተገልጿል።
የጋቦን መፈንቅለ መንግስት ከ2020 ወዲህ በምዕራብና ማዕከላዊ አፍሪካ የተደረገው ስምንተኛው መንግስት ግልበጣ ነው።
የጋቦን መፈንቅለ መንግስት በመንግስቱ ድርጅት፣ በአፍሪካ ህብረትና በሀገሪቱ የቀድሞ ቅኝ ገዥ ፈረንሳይ ተወግዟል።