ጋቦን 70 በመቶ ገቢዋን ከነዳጅ ሽያጭ የምታገኝ የአፍሪካ ሀብታም ሀገር ተብላለች
ጋቦን ካላት መሬት ውስጥ 88 በመቶው በደን የተሸፈነ እንደሆነ ተገለጸ።
ማዕከላዊ አፍሪካዊቷ ሀገር ጋቦን ከሰሞኑ በተፈጸመ መፈንቅለ መንግሥት የዓለምን ትኩረት ስባለች።
ሶስት ሚሊዮን የማይሞላ ህዝብ ያላት ጋቦን 88 በመቶ ህዝቧ በከተሞች እንደሚኖሩ ተገልጿል።
ጋቦን በነዳጅ ሀብቷ፣ በማግኒዢየም እና በደን ሀብቷ በአፍሪካ ታዋቂ ሀገር ስትሆን ከአህጉሪቱ የተሻለ ኢኮኖሚ ካላቸው ሀገራት መካከልም አንዷ ናት።
ሀገሪቱ ከውጭ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ውስጥ ነዳጅ የ70 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን የንግድ ገቢዋን በሌሎች ምርቶች እንድትደጉም አለም ባንክ አሳስቧል።
268 ሺህ ስኩየር ኪሎ ሜትር ስፋት ያላት ጋቦን 88 በመቶው መሬቷ በደን የተሸፈነ እንደሆነ ተገልጿል።
ይህን ተከትሎም ጋቦን በካርበን ጋዝ ልቀት መጠን ስኬታማዋ ሀገር የተባለች ሲሆን የተመድን የካርበን ጋዝ ክፍያ በማግኘትም ቀዳሚዋ ሀገር ነች።
የደን ሀብታም ሀገር መሆኗን ተከትሎም እንደ ጉሬላ፣ ዝሆን፣ ነብር እና ሌሎች ብርቅዬ የዱር እንስሳት ባለቤት ሀገር መሆኗ ተገልጿል።
ከአምስት ጋቦናዊያን ውስጥ አራቱ በከተሞች የሚኖሩ ሲሆን የሀገሪቱ መዲና ሊበርቪል እና ፖርት ጀንቲል ከተሞች ከሀገሪቱ ዜጎች ውስጥ የ60 በመቶ መኖሪያ ከተሞች ናቸው።
በሱስ የተጠቁ ሰዎችን የህክምና ድጋፍ ለማድረግ የሚያገለግለው ኢቦጌን የተሰኘው እጸዋት በጋቦን የሚገኝ ሲሆን በህገወጥ መንገድ ወደ ተለያዩ ሀገራት እንደሚዘዋወር ይታመናል።
ይህ እጽዋት አነቃቂ ኬሚካል አለው በሚል አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎች የአውሮፓ ሀገራት ይህ ዕጽዋት ወደ ሀገራቸው እንዳይገባ አግደዋል።