ፑቲን የኒጀር ውጥረት በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቀዋል
የኒጀር ጁንታ መንግስት ግልበጣውን ተከትሎ የተደቀነውን ቀጣናዊ ቀውስን ለመፍታት ፈቃደኛ መሆኑን አስታውቋል።
በጁንታው መንግስት የተሰየሙት "ጠቅላይ ሚንስትር" ዜይን ለንግግር ፈቃደኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።
"በሽግግር ሂደት ላይ ነን፤ በተደጋጋሚ ይህን ስንገልጽ ነበር። ከሁሉም ወገኖች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኞች ነን፤ ነገር ግን ሀገሪቱ ነጻ እንድትሆን አስፈላጊ መሆኑን አበክረን ተናግረናል" ብለዋል ።
የአፍሪካ መንግስታትና ምዕራባዊያን መፈንቅለ መንግስት አቀነባባሪዎች ፕሬዝዳንት ባዙምን ወደ ስልጣናቸው እንዲመልሱ በተደጋጋሚ ወትውተዋል።
ከሦስት ሳምንታት በፊት ስልጣን የተቆጣጠሩት የኒጀር ወታደራዊ መሪዎች ጥያቄዎችን ውድቅ በማድረግ፤ ለንግግር በራቸው ዝግ መሆኑን ሲናገሩ ቆይተዋል።
የምዕራብ አፍሪካ የኢኮኖሚ ማህበረሰብ (ኢኮዋስ) ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ካልተሳኩ በሚል ተጠባባቂ ኃይል እያደራጀ ነው።
የኢኮዋስ አባል ሀገራት የጦር መሪዎች ሊኖር የሚችል ወታደራዊ ጣልቃ-ገብነት ላይ ሀሙስና አርብ በጋና ይመክራሉ ተብሏል።
የሩሲያ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለሳህል ክልል መረጋጋት ሲባል ውጥረቱ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጠይቀዋል።
ፑቲን መፈንቅለ መንግስት አድርጎ ስልጣን ከተቆጣጠሩት የማሊ መሪ ጋር በኒጀር ጉዳይ መክረዋል።
የፑቲን ጥሪ በምዕራብ አፍሪካ ሳህል ክልል ውስጥ እየጨመረ የመጣውን የሩስያን ተጽዕኖ በሚፈሩ ምዕራባውያን ሀገራት ላይ ስጋት ፈጥሯል።