የ”ጌም ኦፍ ትሮንስ” ጸሃፊዎች ቻትጂፒቲን ከሰሱ
በአለም ዙሪያ ተወዳጅ ወደሆነ ተከታታይ ፊልም የተቀየረውን መጽሃፍ የጻፉት ደራሲዎች የቅጂ መብታችን አልተከበረም የሚል ክስ ነው ያቀረቡት
የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የጥበብ ስራዎችን ያለፈቃድ እየወሰደ ነው በሚል ትችት እየቀረበበት ነው
የ”ጌም ኦፍ ትሮንስ” መጽሃፍ ደራሲዎች የቻትጂፒቲ ባለቤት የሆነውን ኦፕንኤአይ ኩባንያ መክሰሳቸው ተሰምቷል።
አሜሪካዊያኑ ጸሃፊዎች ጆርጅ አርአር ማርቲን እና ጆን ግሪሻም በማንሃተን በሚገኝ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ያቀረቡት ክስ ቻትጂፒቲን ለማሰልጠን መጽሃፍቶቻችን ያለፈቃዳችን ጥቅም ላይ ውለዋል የሚል ነው።
ቻትጂፒቲን ጨምሮ የሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂዎች የጥበብ ስራዎችን ባለቤትነት በመንጠቅ ላይ ናቸው የሚሉ ተደጋጋሚ ቅሬታዎች እየቀረቡ ይገኛሉ።
ወደ ተከታታይ ፊልምነት ተቀይሮ በመላው አለም ተወዳጅ ተከታታይ ፊልም የሆነው “ጌም ኦፍ ትሮንስ” (“የስልጣን ሽኩቻ”) መጽሃፍ የሰው ሰራሽ ቴክኖሎጂ ሰለባ ከሆኑት የጥበብ ስራዎች አንዱ ሆኗል ተብሏል።
ደራሲዎቹ በቻትጂፒቲ ባለቤት ኩባንያ ኦፕንኤአይ በመሰረቱት ክስ “ፈቃዳችን ሳንጠየቅ ስልታዊ ስርቆት ተፈጽሞብናል” ብለዋል።
ኦፕንኤአይ በበኩሉ የጸሃፊዎችን መብት እንደሚያከብርና ከሰው ሰራሽ አስተውሎት ቴክኖሎጂው ተጠቃሚ እንዲሆኑ እንሰራለን የሚል ምላሽ መስጠቱን ሬውተርስ ዘግቧል።
ኩባንያው በመላው አለም ከሚገኙ በርካታ ጸሃፊዎች ጋር በቴክኖሎጂው ላይ ባላቸው ስጋትና ሁሉንም ተጠቃሚ የሚያደርግ ስርአት ለመዘርጋት በሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ እየተወያየ መሆኑንም ገልጿል።
ይሁን እንጂ ቻትጂፒቲን ጨምሮ ሌሎች የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂዎች የመጽሃፍ ዳሰሳ እና ግምገማ እንዲያደርጉ የጸሃፊዎች ፈቃድ ሳይጠይቅ እንዲሰለጥኑ ይደረጋል ነው የተባለው።
በሰው ሰራሽ አስተውሎት የጥበብ ስራችን ያለአግባብ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው ያሉ ጸሃፍትም ክስ ማቅረብ ከጀመሩ ሰነባብተዋል።
ቴክኖሎጂው የቅጂ መብትን አለማክበሩ በስፋት ይነሳ እንጂ ከስራ የሚያስወጣው የሰው ሃይል ብዛት ይበልጥ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።